Wednesday, May 25, 2016

ዓለምአቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር እና የእንግሊዝ መንግስት ለድርቅ ተጎጂዎች እርዳታ አበረከቱ

ግንቦት ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በድርቁ የተጎዱትን ሰዎች ሕይወት ለመታደግ ዓለምአቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር 35 ሽህ ለሚሆኑ ቤተሰቦች የምግብ፣ የውሃ፣ የጤና አገልግሎት፣ የቤት እንስሳት እንክብካቤ፣ ለሕጻናት ምገባ መርሃ ግብር የሚውል 2.2 ሚሊዮን የስዊዘርላንድ ፍራክ መድቧል።

ለቀጣይ አምስት ዓመታት በሚዘልቀው የቤተሰብ ምገባ ፕሮግራም ማእቀፍ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ለአንድ ሰው በነፍስ ወከፍ 12.5 ኪሎ ግራም በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ ሁለት ሊትር የምግብ ዘይት እርዳታውን ማከፋፈል መጀመሩን ማኅበሩ አስታውቋል።

በአካባቢው ያለው ከ40 ዲግሪ ሰልሺየስ በላይ ሙቀትን ለመከላከል ድንኳኖችን በመትከል ከዓየር ንብረቱ ጋር በመታገል በፈቃደኝነት አገልግሎት መስጠት መቀጠላቸውን የማኀበሩ ሰራተኛ ማሪዮ ሌፓኔን አስታውቀው ፣ በቀጠናው የድርቅ ጉዳተኞች በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች አርብቶ አደሮችና በእንስሳት ተዋጽኦ የሚኖሩ በመሆናቸው በድርቁ ሳቢያ የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን የተረፉትም ግጦሽ በማጣታቸው አደጋው መባባሱን የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች የገጠማቸውን የሕይወት ተግዳሮቶች በምሬት ተናገረዋል። ይህን የከፋ ሁኔታ ተቋቁመው እንደዚህ ዓይነት ስፍራ ላይ መኖራቸው አስገርሞኛል። ከዚህ የበለጠ እገዛና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ሌፓኔን አክለው መናገራቸው ዓለም ቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር በድረ ገጹ አስነብቧል።
የእንግሊዝ መንግስት በበኩሉ በድርቁና በጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን ዜጎች በዘጠኝ ቻርተር አውሮፕላኖች የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ ስራ መስራቱን አስታውቋል። ጎርፉን ተከትሎ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፍናቀሉ ከ150 ሽህ በላይ ዜጎች አፋጣኝ የሆነ የጤና አገልግሎት መስጠቱንም ገልጿል።
ከሰላሣ ሽህ በላይ ለሚሆኑት ዜጎች መጠለያ መስራታቸውንም ያስታወቀው መንግስት፣ ከ10.2 በላይ ዜጎች ለርሃብ አደጋ መጋለጣቸውንና በተለይ ሕጻናት በምግብ እጥረት ቀዳሚ ተጠቂዎች መሆናቸው አሳሳቢ ነው ብሎአል።
ኢትዮጵያዊያን በድርቅ ሳቢያ የመኖር ያለመኖር ትንቅንቅ ባሉበት ሚሊዮኖች ተርበውና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ዕርዳታ በሚያደርግበት ወሳኝ ሰዓት፣ ገዥው ፓርቲ ለግንቦት ሃያ ፈንጠዝያ ድንኳኖችን በመትከል በፌሽታ እያከበረ መሆኑ ከእያቅጣጫው እየተወገዘ ነው።

No comments:

Post a Comment