Tuesday, May 31, 2016

በደቡብ አብዛኛው አርሶአደር የታጠቀው መሳሪያ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ሲሆን በአማራ ክልል የእዝ ቁጥጥሩ የጠበቀ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ


ግንቦት (ሃያ ሦስ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወይም ሜቴክ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የጸጥታ ሃይሎችን ለመለየት እንዲያስችል በሚል በደቡብ እና በአማራ ክልሎች በ2006 ዓ.ም ያደረገው ጥናት ዝርዝር ለኢሳት የደረሰ ሲሆን ፣ ጥናቱ እንደሚያሳዬው በደቡብ ክልል አብዛኛው አርሶአደር የታጠቀው  ዘመናዊ መሳሪያ ክላሽ ሲሆን፣ ይህ የጦር መሳሪያ ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ውጭ ነው።

“የፖሊስና የሚሊሻ ሃይል ከታጠቅው በህብረተሰቡ የታጠቀው የተሻለ በመሆኑ በፀጥታ ሃይሎች ላይ አደጋ አየደረሰ መሆኑን” ሪፖርቱ አመልክቶ፣ ትጥቅ ለመመዝገብ ቢፈለግም፣ አብዛኛው ህዝብ የማስመዝገብ ፍላጎት እንደሌለው ይገልጻል።

በክልል  ፖሊስ እና የደቡብ ክልል ፈጥኖ ደራሽና ፀረ-ሽምቅ ሃይሎች እጅ  5117 መሳሪያ ሲኖር ፣ አጠቃላይ የጸጥታ ሃይሉ ብዛት ግን  11293 ነው። አብዛኛው የጸጥታ ሃይል  በቂ መሳርያ ስለሌለው ጥበቃውን የሚያካሂደው በዱላ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።
ወደ ክልሉ የሚገባው መሳሪያም ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ እንደሚመጣ ሪፖርቱ ይጠቁማል።
በአማራ ክልል የትጥቅ እጥረት እንዳለ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ በክልሉ በአጠቃላይ 184 ሺ ልዩ ሚሊሺያ፣ከ 20 ሺ  በላይ ተጠባባቂ ሃይል እንዲሁም 12 ሺ ፖሊሶች አሉ።
በክልሉ እስከ 2006 ዓም 158 ሺ 918 የግል የጦር መሳሪያዎች ፣ 92 ሺ 671 የመንግስት የጦር መሳሪያዎች አሉ። በግለሰብ እና በመንግስት ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች መካከል ከ70 ሺ በላይ የሚሆነው ሁዋላ ቀር የሆኑና አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው።
መከላከያ ሚኒስቴር ለሜቴክ እንዲሰሩ ወይም እንዲገጣጠሙ የላካቸውን የጦር መሳሪያዎች ዝርዝር በተመለከተም ኢሳት መረጃ የደረሰው ሲሆን፣ መረጃውን በኢሳት ፌስ ቡክ አካውንትና በድረገጹ የሚለቀው ይሆናል። መረጃው መንግስት ያሉትን የታንኮች ፣ የመድፎችና ሌሎች መሳሪያዎችን አይነት እንዲሁም በአጠቃላይ የአገሪቱን የመሳሪያ አቅም የሚያሳይ ነው።



No comments:

Post a Comment