Saturday, May 7, 2016

በድሬዳዋ ጎርፍ የሰው ህይወት አጠፋ ፥ ንብረት አወደመ


ኢሳት (ሚያዚያ 28 ፥ 2008)
ሃሙስ ምሽት በድሬዳዋ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተን የጎርፍ አደጋ ተከትሎ በትንሹ የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው በሃገሪቱ መከሰት የጀመረው የጎርፍ አደጋ የእርዳታ እህል አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን በማሳደር ድርቁ እንዲባባስ ማድረጉን ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ደርሶ በነበረ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ ጉዳት ደርሶበት ነበር የተባለውና ከተማዋን ከመልካጀብድ የሚያገናኝ ድልድይ በዚሁ ጎርፍ ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑንም የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ አመልክቷል።
ከሞቱት ሶስት የከተማ ነዋሪዎች በተጨማሪ ሶስት ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 120 ሜትር ርዝመት ያለው የጎርፍ መከላከያ ግድብም መፍረሱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
በከተማዋ እየተባባሰ የመጣውን ይህንኑ የጎርፍ አደጋ ተከትሎም የድሬዳዋ ዋና የገበያ አካባቢ የንግድ እንቅስቃሴ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
የከተማ ነዋሪዎችን ከቀጣይ አደጋዎች ለመታደግም የውሃ መጠን ሲጨምር የጸጥታ ሃይሎች የመሳሪያ ተኩስን በማሰማት ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲወስድ እንደሚደረግም የከተማዋ አስተዳደር አመልክቷል። ከሁለት ሳምንት በፊት በጅጅጋ በደረሰ ተመሳሳይ የጎርፍ ደጋ ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ አሁን የተከሰተው ጎርፍ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት የእርዳታ እህልን ለተረጂዎች ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ችግርን ፈጥሮባቸው እንደሚገኝ ገልጿል።
በተለይ በሃገሪቱ ምስራቃዊ አካባቢዎች በመጣል ላይ ያለው ከባድ የጎርፍ አደጋ በሶማሊ ክልል የሚደረገውን የእርዳታ አቅርቦት አስተጓጎሎ እንደሚገኝ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። በድርቅ ጉዳት የደረሰባቸው እንስሳትም በዝናቡና በጎርፍ አደጋው እየሞቱ መሆናቸውን የእርዳታ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment