Friday, May 13, 2016

በጄኒራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ የአባይ ግድብ ግንባታን በሶስተኛ ኩባንያ እያሰራ ነው


ግንቦት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተከፍሎት ከ10 የስኳር ኮርፖሬሽን ፋብሪካዎች መካከል አንዱንም ማጠናቀቅ ያልቻለው የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ለአባይ ግድብ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውን ለመስራት ኮንትራት ቢወስድም፣ ሰራውን መስራት ባለመቻሉ የውጭ ኮንትራክተር ቀጥሮ እያሰራ ነው። የውጭ ኩባንያዎች በአማካሪ ስም ቢቀጠሩም ዋናውን ስራ የሚሰሩት እነሱ ናቸው።
አዳማ የእርሻ መሳሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ አዳማ ጋርመንት ኢንዱስትሪ፣ አቃቂ ቤዚክ ሜታልስ ኢንዱስትሪ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ፣ የኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ማሽነሪ ንኡስ ኢንዱስትሪ፣ ደጀን አቪየሺን ኢንደስትሪ፣ ኢትዮ ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ፣ ጋፋት አርማመንት ኢንዱስትሪ፣ ሃይቴክ ኢንዱስትሪ፣ ህብረት ማኑፋክቸሪንግ እና ማሽን ግንባታ ኢንዲስትሪ፣ ሆሚቾ አሙኔሽንና ኬሚካል ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ፣ የብረታብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ፣ ኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የነዳጅና ፕሮፒላንት ንኡስ ኢንዱስትሪ፣ የኳሊቲ ኢንጂነሪንግ ማእከል፣ የሎኮሞቲቭ ንኡስ ኢንዱስትሪ የተባሉ በቀድሞ መንግስት የተገነቡ ኢንዱስትሪዎችንና አዳዲሶችንም ጨምሮ የሚያስተዳድረው ሜቴክ “እየተሳሳትንም እንማራለን” በሚል መርህ ከፍተኛ የህዝብ ገንዘብ እያባከነና ለሙስናው እንደ እንደ ሽፋን እየተጠቀመበት ነው።
ግንባታው የተጓተተው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ የሜቴክ ውጤት ሲሆን ፣ በተጨማሪም የባቡር ሎኮሞቲቮችን መገጣጠም፣ የከተማ አውቶብሶችን፣ የቤት መኪኖች፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች መስራት፣ ሞባይልና ቴሌቪዥን መገጣጠም የሚሉ ሰራዎች ሳይቀር ለመስራት ኮንትራት ቢወስድም፣ በምርት ጥራትና በመለዋወጫ አቅርቦት በኩል ከባድ ችግሮች እየፈጠረ መሆኑን ድርጅቱን በቅርብ የሚያዉቁ ሰዎች ይናግራሉ። በየመንገዱ የሚቆሙት በሜቴክ የተገጣጠሙት የከተማ አውቶብሶች በቂ መለዋወጫ ከድርጅቱ ሊቀርብላቸው ባለመቻሉ አብዛኛዎቹ ለመቆም በመገደላቸው ባለቤቶቻቸውን ለኪሳራ ዳርገዋል።

No comments:

Post a Comment