ግንቦት ፳፫(ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወይም ሜቴክ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የጸጥታ ሃይሎችን ለመለየት እንዲያስችል በሚል በደቡብ እና በአማራ ክልሎች በ2006 ዓ.ም ያደረገው ጥናት ዝርዝር ለኢሳት የደረሰ ሲሆን ፣ ጥናቱ እንደሚያሳዬው በደቡብ ክልል አብዛኛው አርሶአደር የታጠቀው ዘመናዊ መሳሪያ ክላሽ ሲሆን፣ ይህ የጦር መሳሪያ ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ውጭ ነው።
“የፖሊስና የሚሊሻ ሃይል ከታጠቅው በህብረተሰቡ የታጠቀው የተሻለ በመሆኑ በፀጥታ ሃይሎች ላይ አደጋ አየደረሰ መሆኑን” ሪፖርቱ አመልክቶ፣ ትጥቅ ለመመዝገብ ቢፈለግም፣ አብዛኛው ህዝብ የማስመዝገብ ፍላጎት እንደሌለው ይገልጻል።
በክልል ፖሊስ እና የደቡብ ክልል ፈጥኖ ደራሽና ፀረ-ሽምቅ ሃይሎች እጅ 5117 መሳሪያ ሲኖር ፣ አጠቃላይ የጸጥታ ሃይሉ ብዛት ግን 11293 ነው። አብዛኛው የጸጥታ ሃይል በቂ መሳርያ ስለሌለው ጥበቃውን የሚያካሂደው በዱላ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።
ወደ ክልሉ የሚገባው መሳሪያም ከደቡብ ሱዳንና ከኬንያ እንደሚመጣ ሪፖርቱ ይጠቁማል።