Sunday, August 3, 2014

‹የፀረ ሽብር ሕጉ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ነው የሚያሰጋኝ›

አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ፣ የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር

የፎርቹን ጋዜጣ አሳታሚ የሆነው የኢንዲፔንደንት ኒውስ ኤንድ ሚዲያ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት እንዲሁም የጋዜጣው ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነው አቶ ታምራት ገብረ ጊዮርጊስ፣

በኢትዮጵያ የግል ፕሬስ ታሪክ ለረዥም ጊዜ የቆየ  ጋዜጠኛ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጥቂት ጊዜ በኋላ በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርቶ በተለያዩ ጋዜጦች የሠራ ሲሆን በተለይ በጦማር፣ በኢንተርፕረነርና በሌሎች ጋዜጦች ላይ ሠርቷል፡፡ የካፒታል ጋዜጣም መሥራች ነበር፡፡ የግል ፕሬሱን ባለሀብቶች እንደ አንድ ኢንቨስትመንት አይተው እንዳይገቡበትና በአብዛኛው የፖለቲካ ውዝግብ አካል ሊሆን የቻለበትን ምክንያት በተመለከተ የማነ ናግሽ ከአቶ ታምራት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- አንተ ጋዜጠኛ ሆነህ መሥራት ስትጀምር በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የግል ፕሬሱ ምን ዓይነት ገጽታ ነበረው?

አቶ ታምራት፡- የግሉ ፕሬስ ለኢትዮጵያ አዲስ ባህል ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መጨረሻ ጊዜ ተጀምሮ ነበር፣ ደርግ አጠፋው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ሲቆጣጠርም እነዚያ የተቋረጠባቸው ሰዎች ነበር የጀመሩት፡፡ አቶ ጌታቸው የሚባሉ ሰው ነበሩ የጀመሩት፡፡ ኢሕአዴግ ሲመጣ ማስታወቂያ ሚኒስቴርም መከላከያ ሚኒስቴርም ፈርሰዋል፡፡ እነዚህን ጨምሮ በፈረሰው መንግሥት የተለያዩ ተቋማት የነበሩ ሰዎች አዲሱ መንግሥት እንደ አፍራሽ፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና አደጋ፣ ገንጣይና ቅጥረኛ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ናቸው የግሉን ሚዲያ የጀመሩት፡፡ የአገር አደጋ ያሉትን አዲሱን መንግሥት መጣል ነበር ዓላማቸው፡፡ በአብዛኛው ፕሮፓጋንዲስት ነበሩ፡፡ መንግሥትም ያንን በውል አጥንቶ ለማቀራረብ ያደረገው ጥረት የለም፡፡ በነፍጥ ያሸነፍናቸው ምሽግ ቀይረው መጡብን በሚል በዓይነ ቁራኛ ነበር የሚያያቸው፡፡ ለነገሩ ሚዲያ ውስጥ የነበሩ ሰዎች የኅብረተሰቡ ነፀብራቅ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ “Rejectionist Constituency” (የሁሉ ነገር መጀመርያም መጨረሻም የመንግሥት ለውጥ ማድረግ አለብን የሚል) ቡድን ተፈጥሯል፡፡ አዲሱ መንግሥት ምንም ሆነ ምንም ቢሠራ ለመቀበል ዝግጁ ያልሆነ ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ የግሉ ፕሬስ የተጀመረው ያለፈው ሥርዓት አካል በነበሩና አዲሱ መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ በሚፈልጉ ሰዎች ነበር ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡ በወቅቱ ደፋርና ጎበዝ ጋዜጠኛ የምትባለው መንግሥትን በማብጠልጠልና በመሳደብ ነው፡፡ የግሉ ፕሬስ አጀማመር በዚሁ መልኩ ነው የሚገለጸው፡፡ ሚዲያው ውስጥ የነበሩ ሰዎችና መንግሥት በዓይነ ቁራኛ ነበር የሚተያዩት፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በተለይ ከምርጫ 97 በኋላና አዲሱ የፕሬስ አዋጅ ከፀደቀም በኋላ ከበፊቱ ጋር ስታነፃፅረው የግሉ ፕሬስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ትላለህ?



አቶ ታምራት፡- ቀደም ሲል ፖሊስ በመኪና ጋዜጠኛን እያሳደደ የሚውልበት ሁኔታ ነበር፡፡ መንግሥት በአጠቃላይ የግል ሚዲያውን ጠላት ብሎ ፈርጆ በጥላቻ የሚያይበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን እንደዚህ አይደለም፡፡ አሁን ቢያንስ የግል ሚዲያውን ሲተች እንኳን አንዳንድ እያለ ነው፡፡ በአብዛኛው ዕውቅና ሰጥቷል ማለት ነው፡፡ የሚያስጠይቅ ነገርም ካለ አሁን በሕግ ነው የምትጠየቀው፡፡ ይኼን ይኼን ስታይ ብዙ የተሻሻለ ነገር እንዳለ ይገባሃል፡፡ ነገር ግን እንዲሀ ማለት አሁን ምንም አሳሳቢ ነገር የለም ማለት አይደለም፡፡ የዚያን ጊዜ ጋዜጣ ውስጥ እስከሠራህ ድረስ የምትጠየቀውና የምትታሰረው ከፕሬስና ከፕሬስ ጋር በተገናኘ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንደሆነ ታውቃለህ፡፡ ትልቁ እስራት ሦስት ዓመት እንደሆነ ትገነዘባለህ፡፡ የተሰላ አደጋ እንድትወስድ ያደርጋል፡፡ ከዚያ ውጪ በምንም እከሰሳለሁ ወይም እጠየቃለሁ የሚል ሥጋትና ፍርኃት የለብህም፡፡ አሁን የተለየ ነው፡፡ በተለይ የፀረ ሽብር ሕጉ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ ነው የሚያሰጋኝ፡፡ ምክንያቱም አንቀጽ 6 አተረጓጎሙ ክፍት ስለሆነ፣ አሸባሪነትን መደገፍና ማበረታታት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ብሎ በማያወላዳ መንገድ ስላልቀረበ፣ ‹‹አሸባሪነትን በመደገፍ፣ በማገዝ፣ በማበረታታት…›› በሚሉ ክሶች ብዙ ዓመት እስር ቤት የማሳለፍ አደጋው ሰፊ ነው፡፡ ይኼ በፊት ያልነበረ አሁን ግን ከእንቅልፍ የሚያባንን ሕግ ነው፡፡ ከፕሬስ ሕጉ ይልቅ በጣም የሚያሰጋኝና እንዳልኩህ አጥንቴ ድረስ ዘልቆ የሚያስፈራኝ የፀረ ሽብር ሕጉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ተመሳሳይ ትችቶች ይሰነዘራሉ፡፡ የግሉ ሚዲያ እንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ገጽታ እንዲይዝ ያደረገው ምንድነው? ከሌላው ሴክተር በተለየ እንዲህ አወዛጋቢ እንዲሆን ያደረገው ምንድነው?

አቶ ታምራት፡- “So much is at stake” [ብዙ ነገር አደጋ ላይ ነው] የሰዎች ሰብዕና፣ ክብር፣ ጥቅምና የድርጅቶች ህልውናና ጥቅም አደጋ ላይ ነው፡፡ እንደዚያ የፖለቲካ ውዝግብ ቢሆን አይገርመኝም፡፡ ምክንያቱም በሚሠራው ሥራ ስህተትን ማጋለጥ፣ ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግና በአደባባይ መተቸት ነው፡፡ ስለዚህ የተጋለጠ፣ እንዲነገርበት የማይፈልገው ነገር የተነገረበት፣ በአደባባይ የተተቸ ቡድንና ግለሰብ፣ ድርጅትና ኩባንያ ግልጽ ነው ደስተኛ አይሆንም፡፡ አንድ ሚዲያ ደጋግሞ መሪዎች ወይም አንድ ድርጅት የማይፈልገውን ሲሠራ በዚያ ድርጅት ሰዎች፣ ደጋፊዎችና አባሎች ዓይን በጠላትነት ሲታይ የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ይኼ እንዳይሆን የሚገዛው ሕግ ብቻ ነው፡፡ አንድ እሱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሚዲያ ውስጥ አስተሳሰባቸውን የመሠረቱ፣ የቆረጡና የደመደሙ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን ቡድን ወይም ያንን ቡድን አንደግፍም አንቀበልም ብለው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን በማንኛውም መንገድ መውረድ አለበት ብለው የሚያምኑና የሚከራከሩ ሰዎች አሉ፡፡ የሚያደርጉት ነገር ፕሮፌሽናል የሆነ የጋዜጠኝነት ሥራ መሥራት ሳይሆን፣ ይኼ የማይፈልጉት ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ከሥልጣን መውረድ አለበት ነው፡፡ በዚህም ከሥልጣን የሚወርድበትን ጊዜ ለማፋጠን እንሠራለን ብለው በዚያ እምነት የሚንቀሳቀሱ ደግሞ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በጠላትነትና በባላንጣነት ቢያዩዋቸው ምንም የሚገርም ነገር አይደለም፡፡ እንዳልኩህ ደግሞ ገና ከአጀማመሩ በአብዛኛው ፕሬስ ውስጥ የነበሩ ሰዎች አዲሱን መንግሥት የማይቀበሉ ናቸው፡፡ አዲሱ መንግሥት ለኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት፣ ብልፅግናና ደኅንነት አደጋና ጠንቅ ነው ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ፣ በዚህ የተነሳ የሁለቱ ግንኙነት በጥላቻና በጥርጣሬ የተሞላ ቢሆን ምንም የሚገርም ነገር አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድም ያነሳኸልኝ ነገር አለ “Rejectionist Constituency” (ምንም ነገር በአዎንታ ለመቀበል ያልተዘጋጀ) ተፈጥሯል ብለሃል፡፡ ይህ በአብዛኛው ከግሉ ፕሬስ ውልደት ጀምሮ እስከ ምርጫ 97 ድረስና በኋላም ይመስላል፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ ከአገር ወጥተዋል፣ ወይም ደግሞ የሥራ መስክ ቀይረዋል፡፡ መንግሥትም አዲስ አዋጅ ይዞ መጥቷል፡፡ ይኼ ዓይነቱ ወገን ቁጥሩ እየቀነሰ መጥቷል ብለህ ታምናለህ?

አቶ ታምራት፡- እሱን ከግምት አልፈህ ለማየት ከፈለግክ የሚቀጥለውን ምርጫ መጠበቅ ነው፡፡ ያለፈው ምርጫ የሚነግርህ ግን ለምሳሌ መድረክ የሚባለው ፓርቲ ነበር፡፡ ባለፈው ምርጫ የተወዳደረ፡፡ መድረክ ‹‹ሪጄክሽኒስት›› አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ነው፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር በምንም ጉዳይ ዓይን ለዓይን መተያየት አልፈልግም ብሎ ሲንቀሳቀስ የነበረ ነው፡፡ የጋራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አልገባም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሥነ ምግባር ደንብ አልፈርምም ያለ ፓርቲ ነው፡፡ ይህንን ስታይ ገዥው ፓርቲ የሚያቀርበውን ነገር በሙሉ ባለመቀበል ላይ የተመሠረተ ፓርቲ ነው፡፡ ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ በፊት አንድ ዓመት ከምናምን በነበረ ሒደት ነው መድረክ የመጣው፡፡ የምርጫውን ካርድ ውጤት ተመልከት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከተሰጡ የምርጫ ካርዶች በሙሉ ኢሕአዴግ ያገኘው 53 በመቶ ይመስለኛል፡፡ ተቃዋሚዎች በድምር 47 በመቶ አግኝተዋል፡፡ ከዚያ 47 በመቶ ውስጥ 83 በመቶ ድምፅ ያገኘው መድረክ ነው፡፡ እነ ኢዴፓና መኢአድ ብዙ ዓመታት የቆዩ፣ ብዙ አባል ያላቸው፣ ታሪክ ያላቸው የ97 ምርጫ ላይ እጅግ ዝነኛ የነበሩ ናቸው፡፡ ብዙ ሰው የሚያውቃቸው ፓርቲዎች ቁጭ ብለው ከአንድ ዓመት ትንሽ በዘለለ ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ መድረክ የሚባል ፓርቲ ለተቃዋሚዎች ከተሰጠ ድምፅ ውስጥ እንዴት 83 በመቶውን አገኘ? እንግዲህ መልሱን የምታገኘው መድረክ የዚያን ጊዜ የተከተለው የራሱን መንገድ ነው፡፡ ኢሕአዴግን ባለመቀበል ላይ የተመሠረተ ስለነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢዴፓና መኢአድ የፓርቲዎች ምክር ቤት አባል ሆነዋል፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡን ፈርመዋል፡፡ መድረክ አልነበረም፡፡ ይኼ አንድ ነገር ይነግርሃል፡፡ ይኼ እንግዲህ ከዚያን ጊዜ በኋላ በምን ያህል ፍጥነት ወዴት ተቀይሯል የሚለውን ለማወቅ ከፈለግክ፣ ከስሜት በላይ ምክንያት ላይና ቁጥር ላይ ተመሥርተህ ለማወቅ መጪውን ምርጫ መጠበቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅንጅትም መድረክም ‹‹ሪጄክሽኒስት›› ፓርቲዎች ናቸው፡፡ መድረክ ግን በምርጫ 2002 የቅንጅትን ያህል ዝናም ድምፅም አላገኘም፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉልበቱ እየቀነሰ መምጣቱን አያሳይም?

አቶ ታምራት፡- በምርጫ 97 ኢሕአዴግ በዝረራ ነው የተሸነፈው፡፡ ስለዚህ ምን አጠያየቀን እንደሚመስለኝ ከ97 ምርጫ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በእጅጉ የተማረ ፓርቲ ቢኖር ኢሕአዴግ ብቻ ነው፡፡ ለራሱ የሚጠቅም ተምሮ ለማስተካከል የሞከረ ፓርቲ ከነበረ ኢሕአዴግ ነው፡፡ በምርጫ 97 ድክመቱ ተምሮ ለማስተካከልና ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር ለመታረቅ ሞክሯል፡፡ ለዚህም መሰለኝ 53 በመቶ ድምፅ ያገኘው፡፡ የሥራው ውጤት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እሱ እንዳለ ሆኖ ግን ከ97 በኋላ ኢሕአዴግ የወሰደው ተቃዋሚዎችን የሚያዳክም ዕርምጃ ነበረ፡፡ ሦስቱ አፋኝ የሚባሉ አዋጆች ማፅደቁ፣ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ አመራሮችን ማሰሩ፣ በአንፃሩ በጥቅማ ጥቅም አባላቱን እስከ አምስት ሚሊዮን ማድረሱና በእነዚህ ነገሮች የፖለቲካ ምኅዳሩን አፍኗል ተብሎ ሲተች ነበር፡፡

አቶ ታምራት፡- የሁለቱም ድምር ውጤት ነው፡፡ የአባላቱ ማኅበራዊ መሠረት እንዲሰፋ የተለያዩ ፖሊሲዎችን አዲስ አበባ ላይ እንዲተገብር ያደረገው እኮ ከ97 ልምድ በመማር ነው፡፡ አንዱን ነጥለህ ለብቻው የምታየው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የግሉ ፕሬስ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ተሳክቶልህ በዚህ የጋዜጠኝነት ሙያና በጋዜጣ ባለቤትነትም ቆይተሃል፡፡ በዚህ ሙያ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምን ትመክራቸዋለህ?

አቶ ታምራት፡- ተሳካልህ የምትለኝ አንተ ነህ እንጂ እኔ ተሳካልኝ አላልኩም፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ከአንተ ጋር ሙያውን የጀመሩ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ከአገር ወጥተዋል፣ ታስረዋል ወይም ጋዜጠኝነትን ትተው ወደ ሌላ ሥራ ተሸጋግረዋል፡፡ አንዳንዶችም ጋዜጠኛ ሆነው ተቀጥረው የሚሠሩ ናቸው፡፡

አቶ ታምራት፡- ከባድ ነው፡፡ እኔ የምሠራበት ሚዲያ ጠባብ ገበያ የሚባል ዓይነት ነው፡፡ እንደ እናንተ ጋዜጣ ለሁሉም የሚቀርብ ዓይነት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለረዥም ጊዜ ይጠቅማል ብዬ የማስበው ፕሮፌሽናል የሆነ ሚዲያ ለማቋቋም ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሆን አይደለም፡፡ ስትጀምረው አካባቢ ያደክምሃል፡፡ ገበያ ውስጥ ገብተህ ተቀባይነት እስክታገኝ ድረስ ወይም ይኼኛው ወይም ያኛው ሊጎትትህ ይሞክራል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይቀር ብዙ ዋጋ ትከፍልበታለህ፡፡ በረዥም ጊዜ ስታየው ዞሮ ዞሮ ጋዜጠኝነት ለምትኖርበት ማኅበረሰብ ጠቃሚ የሆነ መረጃ መስጠት መቻል ነው፡፡ በ‹‹ክላሲካል›› አስተሳሰብ ማዝናናት፣ ማስተማርና ማሳወቅ ነው፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ ማዝናናትና ማስተማር የሚባለው እምብዛም አይስበኝም፡፡ ማሳወቅ ላይ ነው በብዛት ትኩረት የማደርገው፡፡ ለማሳወቅ በምትሞክርበት ጊዜ የምትሰጠው መረጃ ከፖለቲካ ፍላጎትና እምነት በላይ ይሄዳል፡፡ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ አንድ ኩባንያ ወይም የመንግሥት ድርጅት ይኼን ያህል በጀት አውጥቶ እዚህ አካባቢ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊሠራ እያቀደ ነው ብለህ መረጃ በምትሰጥበት ጊዜ፣ በጣም በቀላሉ ኢንሹራንስ የሚሠራ ሰው ውሰድ፡፡ ይኼ ሰውዬ መረጃውን የሚወስደው ከእምነቱ ጋር ስለሚጣጣም አይደለም፡፡ ካሉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ከአንዱ ኮሚሽን ማግኘት አለበት፡፡ ይኼ ኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ የሚሠራ የኢንሹራንስ ኤጀንት የኩባንያውን መሪዎች አግኝቶ ከእሱ ኩባንያ ኢንሹራንስ እንዲገዙ ማድረግ መቻሉ ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ (ኮሚሽኑ) ለዚህ ሰውዬ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ሰውየው ለመዝናናት፣ ለመሳቅ ወይም ደግሞ ከእሱ የፖለቲካ እምነት ጋር ስለሚጣጣም ደስ ስለሚለው አይደለም፡፡ ተግባራዊ መረጃ ነው፡፡ ወደራሱ ጥቅም የሚቀየር መረጃ፡፡

ይህ እንግዲህ ቀላል በሆነ ነገር ላይ ነው፡፡ ትላልቅ በሆኑ ነገሮች ላይ ጠቃሚ መረጃ በጊዜው ከትክክለኛው ምንጭ ሙሉ መረጃ የምታቀርብ ከሆነ መረጃውን የምታቀብለው ሰውዬ ትጥቅ ነው የሰጠኸው፡፡ ይኼ በቂ መረጃ ያለው ሰው በትክክኛ መረጃ ላይ የተደገፈ ውሳኔ ይሰማል፡፡ ይኼን ማድረግ የሚችል ሚዲያ ማቋቋምና በየጊዜው መምራት ወደፊት ተስፋ ያለው ጋዜጠኝነት ነው ብዬ እከራከራለሁ ብዙ ጊዜ፡፡ ምናልባት ተሳክቶልሃል የምትለኝ ከሆነ፡፡ ነገር ግን ይኼ ይመስለኛል ለብዙ ሰው ጥቅም ያለው ምርት የምንሰጠው፡፡ የእኛ ጋዜጣ ይኼኛውን ቡድን ተቃውሞ ያኛውን ቡድን ደግፎ በዚያ ቅኝት የተሰናዳና የተዘጋጀ ነገር አያቀርብም፡፡ ለአንባቢዎቻችን ከዚያ ቅኝት በተለየ መንገድ በፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት የተሰናዳ መረጃ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡ ያ ማለት እኛ በግላችን የምንወደውና የምንጠላው አስተሳሰብ የለም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ርዕሰ አንቀጾችን ስትመለከት ሊብራል (ነፃ) የሆኑ አስተሳሰቦች የሚንፀባረቁበት ነው፡፡ ለምሳሌ ከኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በተያያዘ አገሩ ለውድድር ክፍት መሆን አለበት፣ የውጭ ኢንቨስተሮች በፈለጉት ሴክተር መግባት አለባቸው፣ የመንግሥት እጅ በኢኮኖሚው ውስጥ ትንሽ መሆን አለበት እያልን እንከራከራለን፡፡ ይኼ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው፡፡ ግን ይኼን አስተሳሰብ በተወሰነ ቦታ ላይ ነው እንጂ የምናደርገው በዜና ትንታኔና በፊቸር ላይ እንዲንፀባረቅ አናደርግም፡፡ ይኼ በትልቁ ስትወስደው ‹‹ኮሜርሽያል›› ሚዲያ የሚባለው የሚዲያ ተቋም የሚሠራው ሥራ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ኅብረተሰቡን ይጠቅማል፣ ግን አንድ የሚዲያ ውጤት ነው፡፡ ሌሎች መኖር የለባቸውም ብየ እየተከራከርኩ አይደለም፡፡  

ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ ጋዜጦች የፖለቲካ ናቸው፡፡ አንተ የንግድና ኢኮኖሚ ጋዜጣ ነው እንዲሆን ነው የመረጥከው፡፡ ከሁሉ ተለይተህ እንዴት ወደዚህ ገባህ?

አቶ ታምራት፡- የዛሬ 15 ዓመት ስጀምር ስለኢኮኖሚ የሚዘግብ ምንም የቢዝነስ ጋዜጣ አልነበረም፡፡ እንዳልኩህ ነጋዴ የሚባል አንድ መጽሔት ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ አንድም የሚዲያ ተቋም ዋናው ጉዳዩና ትኩረት ኢኮኖሚና ቢዝነስ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በእኔ አመለካከት አንድ የገበያ ሥፍራ አየሁኝ፡፡ ኢኮኖሚው መንቀሳቀሱ የማይቀር ነገር ነው፡፡ ኢኮኖሚው ደግሞ እያደገ የነበረው በግሉ ሴክተር ነው፡፡ ዛሬ እንደምታየው የአዲስ አበባ መንገዶች በትላልቅ ቢዝነሶች የተሞሉ አልነበሩም፡፡ አብዛኞቹ ትናንሽ የስፔር ፓርት ሱቆችና ኬክ ቤቶች ነበሩ፡፡ አሁን ነው እንዲህ አድጎ ትልልቅ ሆቴሎችን የምታየው፡፡ የግሉ ሴክተር ወደፊት ማደጉ አይቀርምና እሱን ይዞ ለማደግ እኛ ለምን ከዚህ አንጀምርም ብለን ነው የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንተ ጋዜጠኝነትን የጀመርክበት ወቅት ከፍተኛ የፖለቲካ ትኩሳት የነበረበት ነው፡፡ አብዛኞቹ መንግሥትን የሚቃወሙ ነበሩ፡፡ አንተን እንዴት የፖለቲካ ትኩሳቱ አልወሰደህም?

አቶ ታምራት፡- እንዴ ወስዶኛል፡፡ እኔም ለተወሰነ ዓመት እዚያ ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ በፊት ግን ይህን ያህል መንቻካ አልነበርኩም፡፡ ነገር ግን በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ጋዜጠኝነት ስላለው ቦታ በጣም በእጅጉ አስተሳሰቤ የተቀየረው አሜሪካ ሄጄ [በ1980ዎቹ መጨረሻ] በአሜሪካ ጋዜጦች ላይ ሠርቼ፣ ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚሠራ የገባኝ የመሰለኝ ጊዜ ነው ትንሽ ሠልጥኜ ይህንን ወደ አዲስ አበባ ተመልሼ መሥራት አለብኝ ብዬ የወሰንኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አሜሪካ ከመሄድህ በፊትና ከተመለስክ በኋላ የተቀየረው አስተሳሰብህ ምን ነበር?

አቶ ታምራት፡- እንዳልኩህ የጋዜጠኝነት ሚና በኅብረተሰብ ውስጥ ምን እንደሆነ የተለየ አመለካከት ይዤ ነው የመጣሁት፡፡ በፊት ‹‹ሚሊታንት›› የሚባሉ ጋዜጠኞች መካከል ነበርኩ፡፡ ‹‹ሚሊታንት›› ማለት አንድን ነገር ትወዳለህ ትቀበላለህ ሌላ ነገር አትቀበልም፡፡ ስለዚህ ይኼ ነው ትክክል ብለህ ኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ማድረግ መቻል ነው፡፡ ችሎታህና ብቃትህ የሚለካው በዚያ ነው፡፡ አንድን ኅብረተሰብ ወደምትፈልገው ሞገድ (ጽንፍ) ይዘህ መሄድ ነው፡፡ ‹‹ሚሊተንሲም›› የሚመጣው በዚያው ልክ ነው፡፡ ይህ ብቻ ነው እውነት የሌላው በሙሉ ውሸት ነው ብለህ መከራከር ትጀምራለህ፡፡ ወይም በአጭሩ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ለኢትዮጵያ ህልውናና ደኅንነት አደገኛና ጠንቅ ነው ብለህ ታምንና እሱ እንዲቀየር ለማድረግ የተለያየ እንቅስቃሴ አካል ትሆናለህ፡፡ እሱ እንዳልሆነ የገባኝ እዚያ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላ ነው፡፡ ለካ ጋዜጠኝነት እንደማንኛውም ሙያ ዋጋ ያለው ነገር ነው፡፡ ጋዜጠኛ ከመረጃ ጋር ነው የሚታገለው፡፡ አስተያየት እንኳን በምትጽፍበት ጊዜ ዝም ብለህ ከመሬት ተነስተህ ይኼ ደስ ይለኛል፡፡ ይኼንን እጠላለሁ የሚባል ነገር አለ፡፡ መረጃ ላይ የተመሠረተ አስተያየት አለ፡፡ [Informed Opinion]፡፡ አንድ ነገር ትክክል ነው ትክክል አይደለም ብለህ ከመጻፍህ በፊት መጀመሪያ ሙሉ መረጃ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ከዚያ በኋላ የምትጽፈው ነገር ለኅብረተሰቡ ዋጋ አለው፡፡ ዋጋ ያለው ለምንድነው? የማነ የሚያወራውን ነገር የሚያውቅ ሰው ነው ብዬ ስቀበልህ ነው፡፡ ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ የሚዘላብድ ሰው ነው ብየ የምሰማህ ከሆነ ዋጋ አልሰጠውም፡፡

ለምሳሌ አንድ ፎቅ ተደረመሰ እንበል፡፡ ከተማ ውስጥ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አመጣ፡፡ አንድ የታወቀ ብዙ ልምድ ያለው ከተማ ውስጥ ያሉ በርካታ ሕንፃዎች ዲዛይን ያደረገ ለዚህ ፎቅ መደርመስ ምክንያቱን፣ ምን ቢሆን ኖሮ ላይደረመስ ይችል እንደነበር የሚጽፈውንና አንተ የምትጽፈውን ማንበብ በጣም የተለያየ ነው፡፡ ምክንያቱ ያ ሰውዬ ዕውቀት አለው፣ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ነው ብዬ ነው የማነበው፡፡ አንተ ግን ከመሬት ተነስተህ የሆኑ ሰዎችን ስለምትጠላ ይኼ ፎቅ እንዲህ ቢሆን ኖሮ አይደረመስም ነበር ብለህ የምትጽፍ ከሆነ፣ በቃ የራስህ አስተያየት ነው፡፡ እኔ ከሚኖረኝ አስተያየት የሚለይ አይሆንም፡፡ አሁን እኔ ተነስቼ ስለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁመናና ይዞታ ልጻፍ ብል ከዬት አምጥቼ? ለምንስ ነው እኔ የምጽፈው? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ መከላከያ ውስጥ ረዥም ዓመት የሠራ ብዙ ዓመት አገልግሎት የነበረው ሰው ቢጽፍ የእሱ አስተያየት መረጃ አለው (ኢንፎርምድ ነው) ብለህ ስለምታስብ ዋጋ ትሰጠዋለህ፡፡ ልክ እንደዚያ ጋዜጠኝነት ደግሞ ከአስተያየት ውጪ ያለው የሪፖርት ሥራ በሆነ ነገር ላይ ያንተን አመለካከት ነጋ ጠባ ኅብረተሰቡ ጉሮሮ ውስጥ መሰንቀር አይደለም፡፡ እኔ ባለኝ ግንኙነት መታጠር ምክንያት ከተማው ውስጥ እኔ የማላውቀው ብዙ ነገር አለ፡፡ አንተ ግን ገንዘብ መድበህ ልምዱም አለኝ ብለህ ምን እንደተደረገ ፈልገህ ትነግረኛለህ ነው፡፡ ስለዚህ ያንተን አስተሳሰብ አይደለም የምፈልገው፡፡ ያለህን ዕውቀትና ገንዘብ ተጠቅመህ አዲስ ነገር ትነግረኛለህ ብዬ ነው የማስበው፡፡ እሱ ላይ ተመሥርቼ ትክክለኛ ውሳኔ መስጠት ይረዳኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራ መሥራት የሚችል ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ እዚህ ከተማ ውስጥ ማፍራት ቅዥት ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ቀደም ብለህ ነካክተኸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የግል ፕሬስ በፕሮፓጋንዲስቶች ነው የተጀመረው ብለኸኛል፡፡ እስቲ በፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነትና በ‹‹አክቲቪዝም›› (አቀንቃኝነት) መካከል ያለውን ርቀትና ቅርበት አስረዳኝ?

አቶ ታምራት፡- ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ መሆንና ‹‹አክቲቪስት›› መሆን ለየቅል ነው፡፡ ሁለቱም የሚዛባ የሚመስለኝ ለምን መሰለህ? ‹‹አክቲቪዝም›› ሐሳብን በመግለጽ ነፃነትና መብት ሥር ውስጥ ነው ያለው፡፡ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት እንደዚሁ ሐሳብን በመግለጽ ነፃነት ሥር ነው ያለው፡፡ ሁለቱም የሰው ልጅ መሠረታዊ የሆነው መብት ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ ‹‹አክቲቪስት›› መሆን የለብህም ብለህ አትከራከርም፡፡ ‹‹አክቲቪስት›› ለመሆን ግን ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ መሆን አያስፈልግህም፡፡ የሆነ ነገር ማመን መቻል ነው፡፡ እሱን አምነህ ደግሞ እምነትህን የምታሰራጭበት መንገድ መፈለግ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ለመሆን ብቃት ይጠይቃል፣ ልምድ ያስፈልግሃል፡፡ ችሎታ ካለ ገንዘብ ያስፈልግሃል፡፡ ምክንያቱም መረጃ በምታሰባስብበት ጊዜ ዝም ብለህ ቢሮ ቁጭ ብለህ አይደለም እያመጡ የሚመግቡህ፡፡ ያለበት ቦታ ስትሄድ ወጪ ይጠይቅሃል፡፡ ጋምቤላ ውስጥ የሆነ ነገር ተፈጠረ በሚባልበት ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ቁጭ ብለህ አይደለም የምትጽፈው፡፡ ጋምቤላ ከሄድክ ደግሞ መዓት ወጪ አለ፡፡ የእነዚህ ሁሉ ውጤት ነው ጋዜጠኝነት፡፡

‹‹ኢክቲቪዝም›› ግን ጋምቤላ የተፈጸመው ትክክል ነው ትክክል አይደለም ብሎ ለመጻፍ ከቤትህ እግርህን ማንሳት የለብህም፡፡ ዝም ብለህ ከመንግሥት ሚዲያ ወይም እዚያ ደርሰው ከመጡ ሰዎች ወይም በስልክ ከምትሰማው አስተሳሰብ ትቀርፃለህ፡፡ በዚያ አስተሳሰብ ለዚህ ምክንያቱ እነ እከሌ ናቸው ብለህ ቁጭ ብለህ መክሰስና መጻፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በፊትም አሁንም ሁለቱም እጅግ ተደበላልቀዋል፡፡ ተጠቃሚው ኅብረተሰብ ያለው ግንዛቤም በጣም የተደበላለቀ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ትክክለኛ፣ ቆራጥና ደፋር ጋዜጠኛ ማለት የማይፈራ አድርገው ያስባሉ፡፡ እንዲህ ለሚያስቡ ሰዎች ያለኝ ክብር እንዳለ ሆኖ እኔ ግን ጋዜጠኝነት የሚሰጠውን የሚጠብቁ ሰዎች በትክክል አገልግሎቱን ያገኛሉ ብዬ አላምንም፡፡ ‹‹አክቲቪስቶች›› የሚጽፉትንና የሚሉትን የማመን መብት አላቸው፡፡ በጊዜው የሚቀርብ፣ ያልተደበላለቀ፣ የተጣራና የጸሐፊው ግለሰብ ጣልቃ ገብነት የሌለበት ትክክለኛ መረጃ ያገኛሉ ብዬ ግን አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡-  በመረጃ ላይ ተመሥርቶ የሚቀርበው ሪፖርት ያለውን ፋይዳ ያህል፣ በአሉባልታ ላይ ተመሥርቶ የሚጻፍ ዘገባ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ይህንን መታገስስ አደጋው የከፋ አይሆንም?

አቶ ታምራት፡- የአሜሪካን ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰነው፣ “The best instrument to fight hate speect is more speech” [የጥላቻ ንግግር ለመታገል ብዙ መናገርን መፍቀድ ነው]፡፡ ይኼ የጥላቻ ንግግር ይፈቀድ አይፈቀድ የሚለው ክርክር ነበራቸው፡፡ መጨረሻ ላይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይፈቀዳል ብሎ ሲወስን ያንን ውሳኔ ያነበቡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የተናገሩት ነው፡፡ በመከልከልህ እንዲደበቅ ታደርገዋለህ እንጂ አታጠፋውም፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት መብት የማሰብ ቅጥያ ነው፡፡ ሁለታችን ሰይጣናዊ የሚባል ነገር አስበናል፡፡ አንተ ያንን አስተሳሰብ ለራስህ በመያዝህ ማንም አያውቅብህም፡፡ ስለዚህ ደህና ትሆናለህ፡፡ እኔ ግን ተንቀዥቅዤ ያንን አስተሳሰብ በመናገሬ ጥቃት የሚደርስብኝ ከሆነ ልዩነቱ አንተ ተደብቀህ ትቀጥላለህ፣ እኔ በለፈለፍኩት ልጠፋ ነው፡፡ ስለዚህ በመከልከልና በማገድ አላምንም፡፡ በዚህ መሀል ለሚደርሰው አደጋ ተጠያቂ ማን ነው ለሚለው? አደጋው ምን መሰለህ፣ ዞሮ ዞሮ በሚዲያ የሚመጣ አደጋ ግለሰብ ላይ ነው፡፡ አንድ የኅብረተሰብ ቡድን በወል ስሙ ይጠፋል ብዬ አላምንም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጣም ጽንፍ በያዘ ኃይል፣ አንድ የኅብረተሰብ ቡድን ያልሆነ መረጃ ይዞ በሌላኛው የኅብረተሰብ ቡድን ላይ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በዚያ ምክንያት እውነተኛ አደጋ ሊመጣ ይችላል፡፡ እንደሱ በሚሆንበት ጊዜ አገር ውስጥ ሕግ አለ፡፡ በዚያ ሕግ መዳኘት መቻል ነው እንጂ፣ አንድ ሰው ጋዜጣ ላይ አንብቦ ሌላ ሰው ሲጎዳ አይቼ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ በሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ጊዜ ሬዲዮ ሚል ኮሊንስ የተባለ ጣቢያ የተጫወተውን ሚና መካድ አይሆንም?

አቶ ታምራት፡- የሩዋንዳ ጉዳይ ከሆነው በላይ ለሆነ የፖለቲካ ግብ እየተጋነነ የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡ መርሳት የሌለብን ሩዋንዳ ውስጥ መንግሥት ፈረሰ፡፡ ይኼ ሬዲዮ ጣቢያ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረው የመንግሥት ሚዲያ ነው፡፡ አንድ ኅብረተሰብ የመንግሥት አካል በሚያጣበት ጊዜ የሆኑ ቡድኖች ተነስተው ሌሎች ቡድኖች ላይ የሚያካሂዱት ዘመቻ ይኖራል፡፡ ሥርዓት ባለው አወቃቀር ባለው መንግሥት ሕግን የማስፈጸም ችሎታና ብቃት ባለው ሁኔታ የሚንቀሳቀሱ የግል ሚዲያ ተቋማት የሚያደርሱት ጉዳት ከግለሰብ መልካም ሰብዕና ያለፈ ሆኖ አይቼው አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 20 ዓመታት አይቼ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በ97 ዓ.ም. እንዲህ ዓይነት ሥጋቶች ነበሩ፡፡

አቶ ታምራት፡- ሥርዓት ባለበት አገር ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር አይታሰብም፡፡

ሪፖርተር፡- ሚዲያው በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሌላው ሴክተር አትራፊ ቢዝነስ ሆኖ ባለሀብቶችን የማይስብበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ታምራት፡- መጀመሪያ ሚዲያ እንደ ቢዝነስ አለዚያም እንደ ትንሽ ጀማሪ ቢዝነስ ነው የተጀመረው፡፡ በትንንሽ ብሮች ነው የተጀመረው፡፡ ሁለተኛ የገቡትም ሰዎች ከመንግሥት ጋር በነበራቸው ጥላቻ ወይም ጭቅጭቅ ነበር፡፡ እሱ ነገር ተቀየረና ከመንግሥት ጋር ፍጥጫ ሲጀመር የፖለቲካ አደጋው ከፍተኛ ሆነ፡፡ ባለሀብት እንኳን ገንዘብ አውጥቶ እንደ ቢዝነስ ኢንቨስት ሊያደርግበት ይቅርና በግለሰብ ደረጃ ጋዜጠኛ ሆኖ ተቀጥሮ የሚሠራ ሰው እንኳን በቤተሰብ ስንት ነገር እየተመከረ ነው፡፡ መሀል ላይ ግን በ1990ዎች እንደ ቢዝነስ ኢንቨስት ለማድረግ የሞከሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ባለቤት የነበሩ ሰው፣ እነ አቶ ብርሃኑ መዋና መሰሎች ጋዜጣ የጀመሩ ነበሩ፡፡ እዚህ ላይ የነበረው ችግር የሚመስለኝ የሚዲያው ባህሪ ነው፡፡ ሶማሌዎች ‹‹ቢዝነስ አባት እንጂ አጎት የለውም፤›› ይላሉ፡፡ አንድ ነገር ራስህ ገብተህ ስትሠራበትና ሰው ቀጥረህ ስታሠራበት እኩል አይሆንም፡፡ ለዚህ ይመስለኛል ተቀጭቶ የቀረው፡፡ አሁን በገበያ ውስጥ የቆዩ ሰዎችን ብትመለከታቸው መሥራቾቹ ራሳቸው ጋዜጠኞቹ ስለሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጋዜጠኝነትና ገንዘብ መገናኘት ያልቻሉት ለምንድነው?

አቶ ታምራት፡- በገንዘብ ያስከፍላል ወይ ደግሞ ራስህ በጊዜና በጥረት ብዙ ትከፍልበታለህ፡፡ እስከ መጨረሻ ለመዝለቅ ቁርጠኝነቱ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዩኒቲ ባለቤት ለምሳሌ ዕለታዊ ጋዜጣ ጀምረው ነበር፡፡ ነገር ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ በዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ ነው የቆመው፡፡ የሚዲያ ሥራ እንደ ቢዝነስ እንዲዘልቅ ከፈለግክ በጣም ብዙ ጊዜ መቆየት አለብህ፡፡ እንግዲህ እንደ እኛ ዓይነቶቹ ሕይወታቸውም ነው፡፡ እስከ መጨረሻው ብታተርፍም፣ በኪሳራም፣ በረሃብም፣ በጥጋብም እንሠራዋለን የሚል ከፍተኛ ፍላጎት አለ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቆራጥነትና ፍላጎት ያለው ሚዲያውን እንደ ኢንዱስትሪ ተመልክቶ አትራፊ ይሆናል ብሎ የሚያስብና ፖለቲካዊ አደጋውንም ግድ የለም ብሎ የሚገባ ሰው መጥፋቱ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የእውነት ግን ፍላጎቱ አለ (አንባቢያን) ተፈጥረዋል ትላለህ?

አቶ ታምራት፡- የዛሬ 15 ዓመት እንግሊዝኛ ጋዜጣ ሦስት ሺሕ ኮፒ ማሳተም መቻል ትልቅ ነገር ነበር፡፡ አዲስ ትሪቡን ሦስት ሺሕ ኮፒ ነበር የሚያሳትመው፡፡ ትልቁ ጣሪያ ነበር፡፡ እኔ ኢንተርፕረነር የሚባል ጋዜጣ እሠራ ነበር፡፡ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ኮፒ ነበር የምናሳትመው፡፡ እኛ ሦስት ሺሕ ኮፒ ማሳተም ነበር ህልማችን፡፡ ዛሬ ከስምንት እስከ አሥር ሺሕ በመደበኛነት እናሳትማለን፡፡ ገበያውም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሥራህ ላይ ትልቁ ፈተና የሆነብህ ነገር ምንድነው?

አቶ ታምራት፡- ትልቁ ፈተና አንድ ነገር ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ማግኘት፡፡ እኛ ገበያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ብቃት ያለው ጋዜጠኛ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ሚዲያ ደግሞ ትልቁ ዋጋው፣ ሕንፃው፣ ወንበሩ አይደለም፡፡ የሰው ኃይል ነው፡፡ እንዲህ የሚሠራ ካልሆነ ምርትህ ጥራት ያለው ሊሆን አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ታምራት ጥሩ ደመወዝ ይከፍላል፡፡ ያሠለጥናል፡፡ ግን ሠራተኛን በጣም ያስጨንቃል ይባላል፡፡ የሠራተኛ አያያዝህ እንዴት ነው?

አቶ ታምራት፡- (ሳቅ) እውነት ነው ‹‹ስሌቭ ድራይቭ›› [ሰው የሚበዘብዝ] ይላሉ፡፡ እውነት ይሁን አይሁን… ሥራ መቆፈርም ሆነ መሮጥ፣ መጻፍም ሆነ ማምረት የሦስት ነገሮች ውጤት ነው፡፡ ጊዜ፣ ጥራትና ዋጋ፡፡ እነዚህ ሦስት ነገሮች ሲቀናጁ ነው ሥራህ ዋጋ የሚኖረው፡፡ አንዱን ከበደልክ፣ ካዛነፍክ ሥራህ ለተጠቃሚ የሚጠቅም አይሆንም፡፡ ለምሳሌ ጊዜ ባይኖረኝ ነው እንጂ ጊዜ ቢኖረኝ ከዚህ በተሻለ እሠራው ነበር ብትል ምንም ዋጋ የለውም፡፡ በጊዜህ ሠርተህ ገበያ ውስጥ ምርትህ ተወዳዳሪ መሆን ካልቻለ ዞሮ ዞሮ ቢፈልገውም ከአቅሙ በላይ ስለሆነ አይገዛውም፡፡ ስለዚህ ሦስቱን ነገሮች ማመጣጠን ፈተና ነው፡፡ ለማንም ደስ የሚል ነገር አይደለም፡፡ የምትሠራውን ሥራ በጨረስከው ጊዜ ጨርስ የምትባል ከሆነ ድሮውንስ ምን ያስጨንቃል? ዛሬ ይህን ሥራ ሳትጨርስ እንዳትሄድ ከተባልክ ግን በመጨረሻ ስላሰብህ ያስጨንቃል፡፡ በአንድ ሰዓት ውስጥ አምስት ዘገባ መጻፍ ካለብህ መጻፍ አለብህ፡፡ ነገር ግን አምስቱም ዘገባዎች ጥራታቸውን መጠበቅ አለባቸው ከተባለም ያስጨንቃል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ሥራ መሥራት ፈተና ነው፡፡ አንድ ሚኒስትር ያደረጉትን ንግግር ይዘህ የምታመጣ ከሆነ ጉብዝናህ የቱ ላይ ነው? ያንተ ጎበዝ ጋዜጠኛነትና የእኔ ደካማ ጋዜጠኝነት ልዩነቱ ታዲያ የት ላይ ነው? ለምንድነው አንተ አሪፍ ጋዜጠኛ የምትባለው ታዲያ? ታምራት እንደ አንተ አሪፍ ጋዜጠኛ አይደለም ለምን እባላለሁ?

ሪፖርተር፡- በዚህ ሙያህ እንዲህ ዓይነት ኅብረተሰብ መፍጠር እፈልጋለሁ ብለህ ታስባለህ? ምን ያህል ተፅዕኖ አሳደርኩ ብለህ ታምናለህ?

አቶ ታምራት፡- ሚዲያ ከሌላው ቢዝነስ የተለየ የሚያደርገው የተለያዩ ሰዎች አስተሳሰብን በጥሩም በመጥፎም መቅረፁ ነው፡፡ በምታደርገው ነገር ተወደደም ተጠላም በኅብረተሰብ ላይ ተፅዕኖ ማሳደርህ አይቀርም፡፡ ይህን ያህል ተፅዕኖ አሳደርኩ ብዬ መገመት ይቸግረኛል፡፡ ለምንሠራው ጋዜጣ ቋሚ የሆነ አንባቢ መኖሩ ግን ዋጋ እንዳለው ይነግረናል፡፡ እኛ በሒደት በሰው ላይ ተፅዕኖ ማሳደራችን አይቀርም፡፡ በዚህ አጋጣሚ እንዲኖር የምፈልገው ግልጽ ኅብረተሰብ ነው፡፡ ለብዙ ነገር ግልጽ የሆነ፣ የማይነኩ የሚባሉ ነገሮችን እንኳን የሚጠይቅና የሚመራመር ግልጽ ኅብረተሰብ ቢኖር ደስ ይለኛል፡፡ እሱ እንዲፈጠር የእኛ ጋዜጣ ተፅዕኖ ፈጥሮ ከሆነ ተሳክቶልኛል፡፡ ግን የሆነ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ሚዲያ እንደ አንድ ሴክተር እንዳያድግ ያደረገው የህትመት ዋጋ ነው ይባላል፡፡ አሳታሚዎች ማኅበር መሥርታችኋል፡፡ በተግባር እስካሁን ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ ታምራት፡- አሳታሚዎች ድርጅቶች ናቸው፡፡ ግለሰቦች አሳታሚ መሆን አይችሉም፡፡ እነዚህ አሳታሚ ተቋማት ከሁለት ዓመት ውጣ ውረድ በኋላ ባለፈው ግንቦት ወር ‹‹ዋቢ›› የሚባል የግል ፕሬስ አሳታሚዎች ማኀበር አቋቁመዋል፡፡ ማኅበሩ ተመዝግቦ ፈቃድ ወስዷል፡፡ ከዚህ በፊት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ያቀረበው የህትመት ውል የሚባል ነገር አለ፡፡ በብርሃንና ሰላምና በአሳታሚዎች መካከል የተጻፈ ምንም ውል ኖሮ አያውቅም፡፡ ስለዚህ የማተሚያ ቤቱ ሥራ አመራር ይህንን የውል አሠራር አቀረበ፡፡ የአብዛኞቹ አሳታሚዎች ስሜት ውሉን አንቀበልም አይደለም፣ ብዙዎችን እንቀበላለን፡፡ ግን ሁለት አስቸጋሪ አንቀጾች አሉት፡፡ አንደኛ ለማተሚያ ቤቶች ያልተገባ ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ይኼ በሕገ መንግሥቱ የተከለከለው ቅድመ ምርመራ ተመልሶ የሚያመጣ ነው ብለን እንሟገታለን፡፡ ውሉን የማትፈርሙ ከሆነ አይታተምም ብለው ሞክረው ነበር፡፡ የማኅበሩ አመራሮች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተን መፍትሔ አግኝተናል፡፡ የማተሚያ ቤቱ ሥራ አመራሮች አስገዳጅ እንዳያደርጉት፣ ክርክሩ እንዲቀጥል፡፡ ጋዜጦች አሁንም እየታተሙ ነው ያሉት፡፡ ሁለተኛው ያደረግነው ብርሃንና ሰላም የተወከለበት የጋራ ቡድን ማቋቋም ነው፡፡ የጋራ ቡድኑ በውል ረቂቁ ላይ ክርክር እንዲያደርግ ነው፡፡ በዚህም ሳምንት ሁለቱም ወገኖች የሚደራደሩላቸውን ተወካዮች መርጠው ክርክር ተደርጎ እንደምንፈራረም ተስፋ እናደርጋለን፡፡


No comments:

Post a Comment