[ከመቶ ሰባት ቀናት እስር በኋላ በፍቄ ሰለ እስሩ ስለ ምርመራው እና ስለ ወደፊት ተስፋቸው ከቂሊጦ እስር ቤት የሰደዳት መልዕክት ይቺትና። እኔ ጽሁፉን ሳነብ የመጣብኝ ሃሳብ እነዚህ ሰዎች በርካታ ንጹሃንን እስከዛሬ ማንም ሳያያቸው ሲያሰቃዩ የስቃዩ ሰለባዎች ዘጋቢዎች እና ጋዜጠኞች ካልሆኑ የስቃያቸውን መጠን የሚገልጹት በእንባ እና... ''ተወው... ተወው አይነሳ...'' በሚል ምሬት ብቻ ነበር። አሁን ግን በራሳቸው ጊዜ ዘጋቢዎችን ወደ ማዕከላዊ እያስገቡ እነሆ የኢህአዴግ ''አመራር ጥበብ''ን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሰዕላዊ መግለጫ እየሰጡን ነው።
ኢህአዴግ ሆይ፤ በጥፊ በርግጫ አይገኝም ምርጫ፤ እያልን የበፍቄን ጽሁፍ ሁሉም ሰው ያነበው ዘንድ ይሄው...
‹‹አያ ጅቦ ሳታመኻኝ ብላኝ›› በበፍቃዱ ሃይሉ.7
‹‹ታዲያ ጥፋቴ ምንድን ነው ትላለህ?!››፣ ብሎኛል አንዱ መርማሪዬ ስለዞን ዘጠኝ እና እኔም እራሴ እንደጦማሪም እንደአራማጅ ተራማጅም ሠራሁ የምላቸውን ነገሮች ዝርዝር ነግሬው ሳበቃ፡፡ በኋላ ላይ በእስር ቤት ቋንቋ ከ‹‹አባሪዎቼ›› ጋር መገናኘት ከተፈቀደልን በኋላ ስንጠያየቅ ለካስ ሁላችንም ይቺኑ ጥያቄ ተጠይቀናል፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ የምርመራችንን ሒደት የሚገልፀው ጥያቄ፡፡ ‹‹ተጠርጥረን›› የተያዝንበትን ጉዳይ የሚያረጋግጥ ሥራ ሠርተን ባለመገኘታችን (ወይም ‹‹ባለመናገራችን››) ታዲያ ጥፋትህ ምንድን ነው? ተባልን፡፡ ምርመራው የኛን ነፃ መሆን አለመሆን ለማጣራት ሳይሆን ጥፋት ለማግኘት ነበር፡፡ ብዙዎች ‹መንግሥት ዞን ዘጠኝን ለምን ሁለት ዓመት እንደታገሠው› ግራ በመጋባት ይጠይቃሉ፤ ባሕሪው አይደለምና፡፡ የኢትዮጵያ ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ምኅዳር በቀላሉ እንደገመቱት ተይዘን፣ ተመርምረንና ‹‹ተገኘባችሁ›› የተባልነው ‹‹ የግንቦት 7 [እና ኦነግም ጭምር] አባልነት [ብሎም ግብ አስፈጻሚነት] ›› በሽታ ለተከሳሽነት አብቅቶናል፡፡ ቀጣዩ የክርክር ሂደት ነው፡፡
ከዚያ በፊት ግን ዞን ዘጠኝን በሩቅም በቅርብም የሚያውቁ በግራ መጋባት መልስ እንደሚሹ በማሰብ ይቺን አጭር ማስታወሻ ለመጻፍ ተገድጃለሁ፡፡ የእስራችን ሂደት ምን ይመስላል? የምርመራችንስ? እውን የግንቦት ሰባት አባል ነን? [ታዲያ] ለምን ታሰርን? በቅርቡ እንፈታ ይሆን?
ደቂቅም ይሁን ሊቅ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እውነታ የሚጽፍ ማንኛውም ሰው [ኢትዮጵያ ውስጥ ሳለ] አንድ ቀን እታሰር ይሆን እያለ መስጋቱ አይቀርም ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም በአንድ መጽሐፋቸው ላይ ሰው ነገረኝ ብለው የኢትዮጵያ ሕዝብን በሦስት የመደቡት፡- የታሰረ፣ ታስሮ የተፈታ እና ወደፊት የሚታሰር በማለት፡፡ እርግጥ ዞን ዘጠኝ ‹‹ሐሳቡን መግለጽ ፈርቶ ዝም ያለ ሁሉ እስረኛ ነው›› ብሎ መደምደም ሦስቱም ምድብ አንደኛው ውስጥ ያጠቃልለዋል ‹‹የታሰረ›› በሚል፡፡ ዞን ዘጠኞች ጦማራችንን በከፈተን በሁለት ሳምንት ሲታገድብን እና ሌላ ስንከፍት ግና መጨረሻ ላይ ታጋቾቹ እኛ እንደምንሆን እናውቅ ነበር፡፡ ያንን የሚያረጋግጥ ተደጋጋሚ የደህንነቶች ክትትል እና ምልክቶች ስለደረሱን መታሰራችን ማስደንገጡ ባይቀርም ያልተጠበቀ ግን አልነበረም፡፡
እስሩ በክትትሉ የተገኘነውን ስድስት የዞን ዘጠኝ አባላት እና ሦስት ጋዜጠኛ ጓደኞቻችንን መሆኑን በተለይ የጋዜጠኞቹ [ቢያንስ ለእኛ] ያልተጠበቀ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኋላ ኋላ ስንመለከተው ግን በእኛ አስታኮ እነሱንም ማሰሩ የታሰበበት ዘመቻ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ እኛን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሒደትም ቢሆን በቅጡ የታሰበበት ነበር ሁላችንም (ከአስማማው በቀር) ከቀኑ በ11፡00 ገደማ በያለንበት ስንያዝ አስማማው በማግሥቱ ታስሯል፡፡ ሌሎቻችን ቤታችን በሚፈተሸበት ሰዓት ሕጉ የሚፈቅድበት ሰዓት(12፡00) አልፎ ነበር፡፡ በቁጥጥር ስር ካዋሉን በኋላ የሕገ-ወጥ አያያዝ ሰለባ የመሆናችን ሂደት የሚጀምረው ከዚህ ነው፡፡
ማዕከላዊን በክፉ ስሙ ቀድሞ ለሚያውቀው ሰው ግቢውን መርገጥ በራሱ ልብን ያርዳል፡፡ ሆኖም በልቤ /ጓደኞቼም እንደእኔ ሳይሰማቸው አይቀርም/ አንደኛ እኛ ጸሐፊ እንጂ ወታደር ወይም ሰላይ ባለመሆናች፣ ሁለተኛ መቼም ከበፊቱ የተሻለ ሰብዓዊ አያያዝ ሳይኖርም አይቀርም የሚል የዋህ ተስፋ በማሳደሬ ብዙም አልተሸበርኩም ነበር፡፡ የገባሁ እለት ከታሳሪዎች በተሰጠኝ ማብራሪያ ‹‹ሳይቤሪያ›› መግባቴን አወቅኩ፡፡ ከዚያ የ HRW-They want confession የተሰኘ ሪፖርት ላይ የተፃፉ ነገሮች ሁሉ ትክክል መሆናቸውን ለመረዳት የፈጀብኝ ከአንድ ሳምንት ያነሰ ጊዜ ነበር፡፡
ምርመራ ማዕከላዊ ስታይል
ምርመራ በማዕከላዊ ከብልጠት ይልቅ ጉልበት ይበዛበታል፡፡ መርማሪዎቹ የምርመራ ችሎታቸው ተጠርጣሪውን የተጠረጠረበትን ጉዳይ ከማውጣጣት ይልቅ የምርመራ ችሎታ እንዳላቸው ለማሳመን የሚጥሩበት ጊዜ ይበዛል፡፡ ይህም አልሰራ ሲል ጥፊ፣ ካልቾ፣ ከአቅም በላይ ስፖርት ማሰራት እና ግርፋት ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ ይህ እንግዲህ እኔ ላይ ከተፈራረቁብኝ አምስት መርማሪዎች እና ሌሎችም አብሮ ታሳሪዎቼ ከነገሩኝ የተረዳሁት ነው፡፡ እርግጥ ሌሎች ‹‹እርቃንን ቁጭ ብድግ›› የሰሩ ተጠርጣሪዎችም ገጥመውኛል፡፡ ከባባድ ቅጣት (ወፌ ላላ ግርፋት፣ ጥፍር መንቀል) የደረሰባቸው ሌሎች ታሳሪዎች አብረውኝ የታሰሩ ቢሆንም ይህ የተፈፀመባቸው ግን ወደማዕከላዊ ከመምጣታቸው በፊት ነው፡፡ ከነዚህ መካከል የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሚገርመው በዚህ ዓይነቱ ምርመራ የሰጡት ቃል ለማመሳከርያ ማዕከላዊ መምጣቱ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ወደማዕከላዊ ከመዛወራቸው በፊት ከባድ ቅጣት የተቀጡበትን ቦታ የት እንደሆነ እንዳያውቁ አይናቸው ተሸፍኖ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እሥረኞችም መኖራቸው ነው – የደርግን ‹‹ቤርሙዳ›› ያስታውሳል!
እናም በሚያዋርድ እና ክብርን በሚነካ ስድብ በሚያስፈራ የቤቱ (የማዕከላዊ) ጥላ እና ኃይል በተቀላቀለበት የምርመራ ሂደት የተከሳሽ ቃላችንን ሰጠን፡፡ ቃላችን መቶ በመቶ እውነት አልነበረም፡፡ ጫናው በበረታ ቁጥር መስማት የሚፈልጉትን ‹‹ዓመፅ ለመቀስቀስ ፈልገን›› የመሳሰሉ በራስ ላይ ፈራጅ (Self-incriminating) ሐረጎችን እየተናገርን ነበር፡፡ ያም ግን ለመርማሪዎቻችን በቂ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በሚጽፉበት ሰዓት እያንዳንዷን ‹‹ሠራን›› ያልነውን ሁሉ ሊያስከስሰን በሚችልበት ሁኔታ እየገለበጡ እና እየበጠበጡ ፃፉት፡፡ አንዳንዶቻችን እየተከራከርን ሲያቅተን ፍርድ ቤት ይፍታው ብለን ፈረምን፣ቀሪዎቻችን የቻልነውን ያህል ተደብድበንበት ፈረምን፡፡ ‹‹ከተናገርኩት ቃል ውጪ አንድም ቃል አልፈርምም›› በሚል እስከመጨረሻው ታግሎ የተሳካለት አቤል ብቻ ነበር፡፡
በምርመራው ሂደት የተረዳነው ነገር ቢኖር የማዕከላዊ መርማሪዎች ብቃት (Intelligence) አርጩሜ ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እኔ ምርመራ ሲባል ይመስለኝ የነበረው ፖሊሶች ተጠርጣሪዎችን ፈፀሙ ስለሚባለው ነገር በቂ መረጃ ይዘው ግፋ ቢል ለምንና እንዴት እንደፈፀሙት ማውጣጣት ነበር፡፡ ‹‹ዕድሜ ለማዕከላዊ›› የተረዳሁት ነገር ቢኖር ምርመራ ማለት ለካስ ‹‹የሠራኸው ወንጀል ምንድን ነው?አውጣት!›› ማለት ኖሯል- ማዕከላዊ ስታይል፡፡ ‹‹ነጻ ነኝ›› ቢሉ ሰሚ የለም፡፡ አንዴ ታስረሃል ወንጀል ሊገኝብህ የግድ ነው፤ ካልሆነ ይጋገርብሃል፡፡
አሁን ሳስበው ማዕከላዊ ፈርሶ በሥር-ነቀል ለውጥ እንደገና መቋቋም ያለበት ተቋም ነው፤ ቢያንስ በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛ የምርመራው ሂደት (በራሳችን ጉዳይ እንደተረዳሁት) ትዕዛዝ አስፈፃሚነት ይስተዋልበታል፡፡ ማለትም በመርህ የሚመራ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ምርመራው እውቀት መር አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱን ደህንት አደጋ ውስጥ የሚጥል ጉዳይ በምርመራው ድክመት ሳይታወቅ ሊታለፍ ይችላል፡፡ ይህ ችግር የተከሰተው ደግሞ መርማሪ ፖሊሶቹ ከብቃት ይልቅ ለታዛዥነት የተመቹ ታማኞች ሆነው በመመልመላቸው ነው፡፡
‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ››
በምርመራው ሂደት የተጨቀጨቅነውም ሆነ ተገድደን የፈረምነው ጽሑፎቻችንን የበይነ መረብ ዘመቻዎቻችንን፣ የወሰድናቸው ስልጠናዎችም ሆኑ አንዳንዶቻችን የሰጠናቸው ስልጠናዎች አመፅ ለማስነሳት መሆኑን ‹‹እመኑ›› በሚል ስለነበር የጠበቅነው ግፋ ቢል በወንጀለኛ መቅጫው አንቀጽ 238 ወይም 257 ሊከሱን አስበው ነው ብለን ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የክስ መዝገቡ ሲመጣ ‹‹ሽብር›› ያውም ከአስራ አምሰት ዓመት እስከ እድሜ ልክ የሚያስቀጣ አንቀጽ 4 መሆኑን ሳውቅ በበኩሌ ሳቄ ነበር የመጣው፡፡
ማስረጃ ተብለው ከክስ መዝገቡ ጋር የተያያዙት በአብዛኛው ጽሑፎቻችን፣ የዘመቻዎቻችን፣ የጋዜጣ መግለጫዎች እና በተለያዩ ሥልጠናዎች ወቅት የተዘጋጁ የሥልጠና መመሪያዎች (Manuals) ናቸው፡፡ ከዚህ በተረፈ ከግንቦት 7 እና ከኦነግ ጋር ያገናኛችኋል የተባልነው በሦስት ‹‹ሰነዶች›› ነው፡፡ አንደኛው ናትናኤል ኢሜይል ውስጥ በጥቅምት 2001 ተልኮለት የተገኘ የግንቦት 7 የዜና መጽሔት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ገና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አዋጁ ሳይወጣ፤ ግንቦት ሰባትም አሸባሪ ከመባሉ በፊት መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛ ሶልያና ቤት ተገኘ ተብሎ እናቷ ‹‹ቤቴ ውስጥ አልተገኘም፣አልፈርምበትም›› ያሉት እና ለግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል ሰራዊት ምልመላ መመዘኛ ሰነድ ነው፡፡ ይህ የሶሊ የዘለቀ አቋም ለሚያውቅ ሙግት አያስፈልገውም፡፡ እኔ እንደውም ትዝ ያለኝ ከመታሰሬ በፊት የትዊተር ፕሮፋይሏ ውስጥ የነበረው ‹‹no for war›› የሚል መፈክር ነው፡፡ ሦስትኛው ደግሞ ማሕሌት ኮምፒውተር ውስጥ የተገኘው የኦነግ ፕሮግራም ነው፡፡ በርግጥ አብረው የተገኙት የሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎች ፕሮግራሞች ማስረጃ ተብለው አለመቅረባቸው መረዳት ብቻ – እሷም ለምን ፕሮግራሙን እንደያዘችው፤ እነሱም ለምን የኦነግን እንደመረጡ ያጋልጣልና የእመኑኝ ሙግት አያስፈልገንም፡፡ በመሰረቱ ሦስቱንም ‹‹ሰነዶች›› መያዝ ከቡድኞቹ ጋር ግንኙነት መመሥረት የሚሰሩትንም መውደድ ማለት አየደለም፡፡ ይህም ለመሪዎቻችን ባይታያቸውም እንኳ ለወገኖቻችን የጠፋቸዋል ብዬ አላስብም፡፡
ሌላውና በአስቂኝለቱ ተወዳዳሪነት የሌለው ውንጀላ ‹‹48 ሺሕ ብር በናትናኤል በኩል ተቀብለው ተከፋፍለዋል›› የሚለው ነው፡፡ ይህ ብር ፤‹‹አሸባሪ›› ከተባሉት ቡድኖች የተወሰደ እንዲመስል በሚያደናግር አገላለጽ የተጻፈ ቢሆንም የክስ መዝገቡ ውስጥ የተያያዘውና ገንዘቡ የመጣበት ደረሰኝ እንደሚያረጋግጠው የተላከው ከARTICLE 19 ነው፡፡ ይህንን ጨምሮ በእስር ላይ ለምትገኝ ጋዜጠኛ ቤተሰቦች መደገፊያ /ለእስረኛይቱም ማበረታቻ/ የተላከ መሆኑን ለመርማሪዎቹ በዝርዝር አስረድተናቸዋል፡፡ ይህንን እያወቁ ውንጀላውን ማኖራቸው እውነትም እኒህ ሰዎች ወንጀለኞች ናቸው ብለው አምነው ሳይሆን ‹‹ከቻልን አደናግረን እናስቀጣቸዋለን (የማይችሉበት ሁኔታ አይታየኝም)፣ካልቻልን ደግሞ በቀጠሮ ጊዜ እንገዛበታለን፣ ነጻ እስኪወጡም ቢሆን በእስር እናቆያቸዋለን›› የሚል ክፉ ምኞት ነው፡፡
… ሳታመኻኝ ብላኝ!
አህዩት ከታች አያ ጅቦ ከላይ ሆነው ወራጅ ውሀ እየጠጡ ነበር አሉ፡፡ ነገር ያማረው አህዩትን ‹‹አታደፍርሽብኝ›› ሲላት ነገሩ የገባት አህይትም ‹‹ሳታመኸኝ ብላኝ›› አለችው ይባላል፡፡ የኛም ነገር እንደዚያው ነው፡፡
ፖሊስ ሲይዘን እኛ ላይ ይህ ነው የሚባል የመክሰሻ መረጃ አልነበረውም፤ እንዲያውም ከስማችን በቀር የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ ከደህንነቶታቸው በአንዱ ልከንላቸው የነበረውን የጽሑፋችንን ስብስብ እንኳን ሳያነቡት ነበር የያዙን፡፡
አሁንም ማስረጃ ብለው ከክስ መዝገባችን ጋር ያያያዙት ቢያንስ በእኔ ግምት ዘጠና በመቶ የሚሆነው ‹‹ሰነድ›› እኛው ነፃ ያወጣናል ብለን የሰጠናቸው ጽሑፎቻችን ናቸው፡፡ በመርማሪዎቻችን ንግግር ውስጥ እኛ ላይ ወንጀል የማግኘት Desperate ፍላጎት አይተናል፡፡ ምናልባትም እንደገመትነው ቢያንስ እስከ 2007ቱ ምርጫ ድረስ ከማኅበራዊ ሚዲያ ገለል እንድንልላቸው ፈልገዋል፡፡ ከዚህ የተሻለም አማራጭ አልታያቸውም ይሆናል፡፡
በእስካሁኑ ሂደት የማዕከላዊን ለገዢው ፓርቲ ወገንተኝነት በዓይናችን አይተን አረጋግጠናል፡፡ ቀጣዩ ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱን በአደባባይ መፈተሽ ይቀረናል፡፡ ለአሁኑ ግን በቅርቡ እንፈታ ይሆን… የሚል ጥያቄ ‹ሕጋዊ› ሳይሆን መላ ምታዊ አማራጮችን እገምታለሁ፡፡
ኢህአዴግ ወይም የኢህአዴግ መንግሥት የሚያዘው ፖሊስ እኛን በቁጥጥር ሥር ሲያውለን ስለወንጀላችን ማረጋገጫ (ጠበቆች Beyond reasonable doubt) እንደሚሉት ዓይነት ባይኖረውም መቼም የሆነች ስህተት ሳላገኝባቸው አልቀርም በሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ወትሮም የተንቦረቀቀ የሚባለው የፀረ-ሸብርተኝነቱ አዋጅ ውስጥ የሚጥለን ነገር በቀላሉ ማግኘት አልቻሉም፡፡ አለመቻላቸው ግን የተነሱበትን እኛን የመክሰስ ዓላማ አላጠፋውም፡፡ የክስ መዝገቡን ሲያዘጋጁ አንድም የረባ ዐረፍተ ነገር ሳይጽፉ ይዘውን ፍርድ ቤት መቅረባቸው በራሱ አንድም የረባ ጥርጣሬና ማረጋገጫ እንደሌላቸው አመላካች ነው፡፡ ቢሆንም በቅርቡ ይለቁናል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ለምን;
1ኛ. ኢህአዴግ በጣም የሚናደድባቸው እና ታሳሪውን በሚያዋርድ መልኩ ካልሆነ በቀር ከማያደርጋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ- አንዴ ያሰረውን ተቺውን ፤ ያውም ብዙ ደጋፊ ያለውን መፍታት ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደልጅ እልህ ይጋባል ማለቴ ነው፡፡ (ይህንን ስል የእስራችንን ኢፍትሀዊነት የተመለከቱትን ጩኸቶች መጥላቴ አይደለም፤ ያለ እነርሱ መንፈሳችን አይጠገንም ነበር፡በአደባባይ የምናመሰግንበት ቀን ይመጣል)
2ኛ. መጀመሪያ የተጠራጠሩበት እና ኋላ የዋጧት ጥርጣሬያቸው፤ ማለትም (ምርጫውን ተከትሎ) አመፅ ማስነሳት በሚሉት ጉዳይ ላይ እቅድ እንደሌለን ቢያምኑም እንኳን ምናልባት እምነታቸው ከተሳሳተ Risk መውሰድ አይፈልጉም፡፡ ( መጀመሪያም የቀለም አብዩት ዶክመንተሪ አዝማሚያ ያስታውሷል)
3ኛ. ምንም እንኳን ዓመፅም፤ሽብርም የማስነሳት ፍላጎትም አቅምም፤ እንደሌለን ቢያምኑም የገዥው ፓርቲ ጠንካራ ተቺዎች መሆናችንን ስለሚያውቁ እና ስላልወደዱልን ፍርድ ቤት በምንመላለስበት ረዘም ያለ ጊዜ ባለው እስር ወቅት ቢያንስ የእስርን ምሬት እንድንቀምሳት ይፈልጋሉ፡፡ ቅጣትን ጨርሶ በነፃ መለቀቅ እንደማለት፡፡
4ኛ. ኢህአዴግ መፍረድ አይፈራም፡፡
No comments:
Post a Comment