Wednesday, August 13, 2014

ኤርትራ የሩሲያን የጦር ልምምድ ልታስተናግድ ነው

በመላኩ ጸጋው
በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች ተከታታይ የጋራና የተናጠል የጦር ልምምድ ያደረገችውን ሩሲያን በቀጣይ በኤርትራ በቀይ ባህር
አካባቢ ልታስተናግዳት መሆኑን “ጊሲካ አፍሪካ ኦንላይን” በአውሮፓ የሚገኙ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ከሰሞኑ
ባሰራጨው ዘገባ ገልጿል። የልምምዱ ዋነኛ ዓለማ በአንድ መልኩ የሩሲያን ጦር ዝግጁነት ለማረጋገጥ እንዲሁም በኤርትራ
ወደቦች አቅራቢያ ሩሲያ ቋሚ የጦር ሰፈርን (Military base) ለማቋቋም መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። እንደ ዘገባው
ከሆነ የሩሲያ የጦር ልምምድ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ኤርትራ ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ በሩስያ እንደ አንድ ስትራቴጂክ
አጋር ሀገር እየታየች መሆኗን ዘገባው አመለክቷል። እንደዘገባው
ከሆነ አሜሪካ በጅቡቲ ቋሚ የጦር ሰፈር ያላት ሲሆን በተለያዩ
ጊዜያትም ከጅቡቲ ወታደሮች ጋር የአየር ኃይልና የባህር ኃይልን
ባቀናጀ መልኩ የጦር ልምምድ ታደርጋች። ጅቡቲ የአሜሪካንን
ጦር ከማስተናገድ ባለፈ በዋነኝነትም የፈረንሳይ የጦር ሰፈር
በመሆን እያገለገለች ነው። ሱዳን በአንፃሩ ኢራን በቀይ ባህር
የሱዳን ምዕራባዊ ግዛት የባህር ኃይል ቤዝ እንድትመሰርት
ለማድረግ እንቅስቃሴ የጀመረች መሆኗን ቀደም ያሉ የዩናይት
ፕሬስ ኢንተርናሽናል UPI ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህ የሱዳን እንቅስቃሴ ግን በእስራኤል አልተወደደም።
ሩሲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ አቅጣጫዎች ተከታታይ የጦር ልምምዶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች። እንደ ዘጋርድያን

ዘገባ ከቀናት በፊት ከሃያ ያላነሱ የጦር መርከቦችንና በርካታ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ባሳተፈ መልኩ በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ
በሚገኘው ጥቁር ባህር ሰፊ የጦር ልምምድ አድርጋለች። ኢተር ታሰ የዜና ወኪል ባሰራጨው ዘገባም ከዚህም በተጨማሪ ሩስያ
በተመሳሳይ መልኩ ከቻይና ጋር በጋራ በመሆን 18 የጦር መርከቦችን ባሳተፈ መልኩ በሻንጋይ አቅራቢያ በያዝነው አመት የጦር
ልምምድ አድርጋለች። በሌላ አቅጣጫ ሩስያ ከቀናት በፊት አንድ መቶ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ባሳተፈ መልኩ በዩክሬን ድንበር
አቅራቢያ ጠንካራ የጦር ልምምድ ያደረገች መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታል።
ኤርትራ አልሸባብን በሶማሊያ በማገዝ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ በመግባት አካባቢያዊ ሰላምን እያወከች ነው በሚል በተባበሩት
መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በኩል ተከታታይ ማዕቀቦች ጥለውበታል። የቀድሞው የቡሽ አስተዳደርም ሆነ የኦባማ
አስተዳደር ኤርትራን ሽብርን በሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ እንድትካተት ያደረጓት ሲሆን በቅርቡም በዋሽንግተን
በተካሄደው የአሜሪካ አፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ከሮበርት ሙጋቤ እና ከአልበሽር ጋር ኢሳያስ አፈወርቂ በስብሰባው ላይ
የሚታደሙበት ጥሪ ሳይደርሳቸው ቀርቷል።ሩሲያ በአንጻሩ ከዩክሬን ጋር በተያያዘ ፖለቲካ ውዝግብ መግባቷን ተከትሎ በምዕራባውያኑ ሀገራት ተከታታይ ማዕቀብ የተጣለበት ሲሆን የሩሲያ መንግስት በአንፃሩ የአውሮፓና የአሜሪካ የግብርና ምርቶች ወደ ሀገሩ እንዳይገቡ እገዳን ጥሏል። የዩክሬኑን ውዝግብ ተከትሎ ሩሲያ ተከታታይ ወታደራዊ ልምምዶችን እያደረገች ሲሆን የቀይ ባህሩም የጦር ልምምድ የዚህአካል ነው ተብሎ ይገመታል። ዘገባውን ያሰራጨው ጊሲካ አፍሪካ ኦንላይን የመረጃ ስርጭቱን በዋንኛነት በኢትዮጵያ፣በኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌላድ፣ ኬኒያ እና ኡጋንዳ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራ የሚዲያ ተቋም ነው።በኢጋድ ዙሪያም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሰፋ ያሉ ዘገባዎችን ሲያሰራጭ ቆይቷል። ዜናው የተገኘው ዛሬ በአዲስ አበባ ታትሞ ከወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ነው።


No comments:

Post a Comment