ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት ነጻነታቸውን አግኝተው የዓለም ቀጣይ ኃያል አገራትን ተቀላቅለዋል፡፡ አብዛኛው የዓለም ማህበረሰብ ዴሞክራሲያዊ በሆኑ ስርዓቶች ለመተዳደር እድል አግኝቷል፡፡ ህወሓት/ኢህአዴግ ግን ስልጣን ከያዘ ማግስት በህግ ፈቀድኩት ያለውን የሚዲያ ነጻነትን ጨምሮ በማፈን፣ በዛው በርሃ ውስጥ በነበረው ‹‹ውርጋጥነቱ›› ቀጥሏል፡፡ አሁንም ቢሆን ‹‹ሲቪል›› ነኝ ብሎ የሚያስበው በአፈሙዝ ነው፡፡ በአንድ በኩል ዴሞክራትነቱን እያስወራ በተግባር ግን የአምባገነኖች ቁንጮ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በአጠቃላይ በርሃ ከነበረበትም በባሰ አሁንም እንዳፈተተው በኢትዮጵያውያን ላይ ስልጣኑን የሚያስጠብቅለትን እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል፡፡ ኢህአዴግ አልተገራም፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ሌሎቹን ስለ መግራት ያወራል፡፡ ትናንትና ማታ (ነሐሴ 19/2006) በልሳኑ ያሳየው ‹‹ያልተገሩ ብዕሮች›› የተሰኘ ፊልም የሚያሳየውም ይህንን ከአለ-አቅም መንጠራራትን ነው፡፡ ኃይሌና ገና በጋዜጠኝነት ተመረቁ የተባሉ ወጣቶች የእነ ፕሮፌሰር መስፍንን፣ የእነ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራን፣ የእነ ተመስገን ደሳለኝን፣ የእነ ዓለማየሁ ገላጋይን ብዕር ‹‹ሊገሩ›› ሲፍጨረጨሩ ማየት በእጅጉ የሚያስገርም ነው፡፡
ሲያሸንፍም በስሜት የዘለልንለት፣ ሲሸነፍ የተሸነፍንለት የድሮው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከስርዓቱ ጋር አብሮ ‹‹ሚዲያ ኑክሊየር ነው!›› ሲል ‹‹አጥፊነቱን›› መስክሯል፡፡ በእርግጥ ኃይሌ በህዝብ ላይ ሲቀልድ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከአመት በፊት በሰይፉ ፋንታሁን የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ስለ መምህራን የደሞዝ ጭማሬ ተጠይቆ የመምህራኖቹ የደምወዝ ጭማሬ ቅብጠት መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከአንድ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ እንዳገኘሁት ከሆነ ኃይሌ ገብረስላሴ ለስርዓቱ አፋኝነትም በግልጽ ድጋፉን እያሳየ እንደሚገኝ ነው፡፡ የመረጃ ምንጩ እንደጠቀሰልኝ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚታጎሩበት የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማስፋፊያ የተሰራው በኃይሌ ገብረስላሴ የገንዘብ እገዛ ነው፡፡ ለዚህ ፖሊስ ጣቢያ ካቴና ከውጭ አገር ያስመጣውም ኃይሌ ገብረስላሴ እንደሆነ ምንጩ ገልጾልኛል፡፡
በርካታ ኢንቨስትመንቶቹ በገዥው ፓርቲ ይሁንታ እንደሚቀጥሉ ያመነ የመሰለው ኃይሌ ትናንትናውም ቢሆን የስርዓቱ መሳሪያ ሆኖ ሚዲያውን ሲተች ያመሸው ከራሱ የኢኮኖሚ ጥቅም አንጻር ነው፡፡ ኃይሌ ከኑክሊየርም በላይ አፍራሽ ነው ያለውን ሚዲያ መተቸት የጀመረው በአንድ ዘገባ ምክንያት አንድ የውሃ ፋብሪካ መዘጋቱን በመግለጽ ነው፡፡ ኃይሌ ይህን ወደ ራሱ አስጠግቶ ሲያጠናክርም ‹‹በእኔ ላይ በመጻፉ ልጆቼ፣ ቤተሰቤ ያያሉ፡፡ በስሬ 1500 ሰራተኛ አለ፡፡ አዋሳ፣ ባህርዳር፣…ያሉት ሰራተኞችም ያዩታል፡፡ ሰራተኞችም ይህ ሰው ምን ነካው ይላሉ፡፡ ቢዝነስ ‹ኮላፕስ› ያደርጋል፡፡›› ሲል ነበር የገለጸው፡፡ እንግዲህ ገና የኃይሌ ልጅ ትሰማለች ተብሎ፣ ሰራተኞቹ ‹‹ምን ነካው!›› ስለሚሉ፣ ‹‹ቢዝነሱ ኮላፕስ›› ስለሚያደርግ ኃይሌ ምንም ያህል ቢያጠፋ ሚዲያው ትንፍሽ ላይል ነው ማለት ነው፡፡ ይህን የኃይሌን ሀሳብ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር ነች የተባለችውም ‹‹የሰዎች ጓዳ (መቼስ ሚስጥር ማለቷ ነው) ሚዲያ ላይ መውጣት የለበትም፡፡›› ስትል ሀሳባቸውን ተሰብስበው የተስማሙበት አስመስላዋለች፡፡ በቃ ሚዲያ ሚስጥር የማውጣት ሚናውን በእነ ኃይሌ ዳኝነት ተቀማ ማለት ነው፡፡ እነ ኃይሌና ዶክተር አሸብር ለስርዓቱ ክንድ በሆኑበት በዛው ፊልም ላይ ካሳ ተከፍሏቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ኃይሌ ገብረስላሴ ሊወዳደር ነው፣ ዶ/ር አሸብር አምባገነን ነው›› የሚሉ ዜናዎችና ትችቶች ሳይቀር በአጥፊነት የተፈረጁላቸው፡፡
ሚዲያ ከሌለው መንግስት ይልቅ መንግስት የሌለው ሚዲያ ይሻላል የሚል መርህ የሚከተሉትን የእንግሊዝና የአሜሪካን ዴሞክራሲ አውቀዋለሁ ያለው ኃይሌ ገብረስላሴ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› በሚል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሚዲያ ‹‹ያልተገራ›› በመሆኑ በሚያሳስብ መልኩ ያ ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰለትን ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ራዕይ›› እናስጠብቃለን የሚሉ አካላት እርምጃ እንዲወስዱ ፍርደ-ገምድልነቱን አሳይቷል፡፡
ስርዓቱን የማዳን እርብርብ
በዚህ ፊልም ላይ ስለ ሰራዊት ፍቅሬ የፍቅር ደብዳቤ መጻፍ፣ በሞቅታ ስለሚጨፍሩት አርቲስቶች አስተያየት መስጠት በአውዳሚነት አስፈርጇል፡፡ ይህ የሆነው እነዚህ ‹‹ልማታዊ አርቲስቶች›› ያልተገራው ስርዓቱ ቅቡልነት እንዲያገኝ ሳይታክቱ የሚሰሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹አባይ ለፕሮፖጋንዳ አይዋል›› ማለት ብሄራዊ ደህንነትን ተጻርሮ የቆመ አስመስሏል፡፡ ከምንም በላይ ስርዓቱ ለስልጣኑ መሰረት አድርጎ የሚወስዳቸው አንጓዎች በሚዲያው ሊነኩ የማይገባ ‹‹ቀይ መስመሮች›› ተደርገው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ መቼም አንድ ተቃዋሚ መንግስትን የተቆጣጠረውን ፓርቲ ከስልጣን አውርዶ መንግስት ለመሆነ ነው የሚሰራው፡፡ ያልተገራው ‹‹መንግስት›› መሳሪያ የሆኑትና እነሱም ከስርዓቱ ጋር በጥቅም ከመጋራታቸው ውጭ የተገራ ነገር ያልታየባቸው ነገር ግን የተገሩትን ሲያጣምሙ የታዩት የፊልሙ ሰሪዎች ግን ‹‹ህዝብ ሌላ መንግስት ለማየት ፍላጎት አለው›› የሚለውን ከኑክሊየርም በላይ አጥፊ ነው ብለው ፈርጀውታል፡፡ ጋዜጠኝነት ‹‹በራዲካል ሮል›› ፖሊሲ የማስቀየር ሚና አለው ብለው ሳይጨርሱ ‹‹የብሄር ፌደራሊዝሙ እርምት ያስፈልገዋል›› የሚልን መካሪ ጽሁፍ በአሉታዊነት ለፈውታል፡፡ የ‹‹ብሄር ፖለቲካው›› ላይ ምንም አይነት ትችት መቅረብ የለበትም አይነት ያልተገራ አቋማቸውን ዳግመኛ አሳይተውበታል፡፡ ጠባብ አለመሆናቸውን ማሳመን ሲያቅታቸው ጠባብነታቸውን የሚተቹትን ሚዲያዎች ያልተገሩ ሲሉ ወርፈዋቸዋል፡፡ እነሱ አንዳንድ ተቋማት ስለ ‹‹መንግስት›› ያወጧቸውን መልካም የሚባሉ ነገሮች አመት ሙሉ እንደማይደጋግሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለ ድህነት፣ የመፈንቅለ መንግስት ስጋትና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያወጧቸውን ሪፖርቶች የግል ሚዲያው እንዳያወጣ ቅድመ ክልከላ አውጀዋል፡፡ ማጎሪያ ቤት ውስጥ ያለውን ስቃይ ማስተባበል ሲያቅታቸው ‹‹ማረሚያ የሚያስፈልገው ማረሚያ ቤት›› የተሰኘን መካሪ ጽሁፍ በህገ ወጥነት ፈርጀውታል፡፡
ኢህአዴግ የውድቀት ዋዜማ፣ ኢትዮጵያ ለምን አሚሶንን ተቀላቀለች? ፍትህ በሌለበት የፍትህ ሳምንት፣ ለአክራሪነት አስተማሪው ማን ነው? ለተሰኙት መልስ መስጠት ሲያቅታቸው፣ እውነት ሆኖ እንቅልፍ ሲነሳቸው በጸረ ሽብር ህጉ አውድ አሸባሪ ብለው ፈርጀዋቸዋል፡፡ በጣም የሚገርመው አብዛኛዎቹ ጽሁፎች በጥያቄ የቀረቡና ኢህአዴግን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሲሆኑ ኢህአዴግ ግን ቀድሞ ‹‹እኔን ነው›› ብሎ ለራሱ ወስዷቸዋል፡፡ ሚዲያው ገለልተኝነቱን እያሳየም ቢሆን እነሱ የአንድ አካል አፈ ቀላጤ ይሉታል፡፡ ለዚህ እንደ ማስረጃ ያቀረቡት ደግሞ ‹‹ማንን እንመን?›› በሚል የወጣን አንድ ጽሁፍ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዶ/ር ብርሃኑንና በረከት ስምዖንን ያፋጠጠ ጽሁፍ ነው፡፡ ከሁለቱ አካላት ማንንን እንመን ተብሎ በማነጻጸሪያነት የወጣውን ይህን ጽሁፍ ራሱን የማያምነው ኢህአዴግ ‹‹እኔን ነው የማያምኑኝ›› ብሎ ጥፋቱን ቀድሞ ወስዶ ‹‹የአንድ አካል አፈቀላጤ ሆነዋል›› ሲል ይከሳል፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ያልተገሩ ብዕሮች›› በሚል የቀረበው ፊልም የኢህአዴግን ፖሊሲ መተቸት ህገ ወጥነት እንደሆነ የታየበት፣ የስርዓቱ ዋና ዋና የስልጣን ማቆያ ፖሊሲዎችን መንካት ስርዓቱን ሊያፈራርሰው እንደሚችል ባልተገራ አንደበት የተነገረበት ፊልም ነው፡፡ በፊልሙ ተዋናይ የሆኑት አካላት እዛው ፊልሙ ላይ ‹‹ፌቨር›› እየተሰራላቸው በትውልዱ ላይ ሲፈርዱ ስርዓቱን ለማዳን እርብርብ ላይ እንደሆኑ በግልጽ ለማየት ተችሏል፡፡ ሁሉንም ነገር ከኢኮኖሚ አንጻር ሲቃኝ ያመሸው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ‹‹ጦርነት ከፈታው ወሬ የፈታው›› በሚል ኃይል በእጁ ለሆነው ያልተገራ ስርዓት በቅኔ እርምጃ እንዲወስድ አሳስቧል፡፡ የስፖርት ጋዜጦች ድረስ ተሂዶ የተደረጉበት ጥቃቅን ትችቶች በህገ ወጥነት የተፈረጁለት ዶክተር አሸብር በግልጽ አገልጋይነቱንና ስርዓቱን ለማዳን የቆመ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ፓርላማ ላይ ኢትዮጵያ ምንም አይነት ጥቅም ሳታገኝ ለጅቡቲ ውሃ የሚለግሰውን አዋጅ ከተቃወሙት መካከል ዶክተሩ አንዱ እንደነበሩ በሚዲያ ተገልጾ የነበር ቢሆንም ዶክተሩ ግን ስለ አዋጁ ያላቸውን ይሁንታ ሲገልጹ ‹‹ከእኛ ጋር ሳይደርስ ለምን አይጸድቅም?›› የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የህዝብ ተወካይ ነኝ ብሎ አንድን ህግ ‹‹ፓርላማ ሳይመጣ ለምን ራሱ ኢህአዴግ አያጸድቀውም›› ማለት ስርዓቱን ለማዳን እርብርብ ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
በአጠቃላይ በፊልሙ ላይ በአሉታዊነት የተፈረጁት ጽሁፎች ቢበዛ መካሪ ቢሆኑ እንጂ ይህ ነው የሚባል ‹‹አለመገራት›› አይታይባቸውም፡፡ ነገር ግን ባለመገራቱ ሳይነካ የሚደነብረውን ስርዓት ይበልጡን የሚያስበረግጉ መሆናቸው የሚያስገርም አይሆንም፡፡
እነ ኃይሌ ዴሞክራሲን አይቼባቸዋለሁ ባሏቸው አገራት ሚዲያ አራተኛ የመንግስት አካል ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሶስቱ የመንግስት አካላትም ሆነ መንግስት ባለመኖሩ አራተኛ መንግስት ሊሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ ይልቅ መንግስት በሌለበት፣ ካልተገራ ዘመናዊ የቤተ መንግስት ወንበዴ ጋር ግብ ግብ የሚገጥም ብቸኛው የመንግስት አካል ሆኖ ለማገልገል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ መንግስትም ሆነ የመንግስት አካላት እንዳይኖሩ የሚፈልገውንና ልጥ ሲያይ እባብ ነው ብሎ የሚደነብር ያልተገራ ስርዓት እጅጉን አስደንብሮታል፡፡ ስለ ተገራና ስላልተገራ ብዕር ይህ ነው የሚባል እውቀት የሌላቸው፣ የማያገባቸው እነ ኃይሌም ያልተገራው ስርዓት ጋር የተጋሩትን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ስርዓቱ በሚዲያው ላይ እርግጫውን በመሰንዘር እራሱን እንዲያድን እርብርብ አድርገዋል፡፡ የእነ ኃይሌ ምክር ስርዓቱ እንደለመደው እንዲራገጥ የሚገፋፋ ቢሆንም ማዳን አለማዳኑንም ሆነ እነሱ በትውልዱ ላይ እየፈጸሙት ያለውን በደል ግን ታሪክ የሚፈርደው ይሆናል፡፡ጌታቸው ሺፈራው
No comments:
Post a Comment