ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በመርካቶ አንዋር መስጊድና በአካባቢው ላይ በተፈጠረ ግጭትና ብጥብጥ፣ አራት የፖሊስ አባላት መሳተፋቸው በፍርድ ቤት ተገለጸ፡፡
ፖሊስ ለሦስተኛ ጊዜ ሐምሌ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዮች ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ማስቻያ ችሎት 14 ተጠርጣሪዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን እያጣራ መልቀቁን ገልጾ በችሎቱ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ላይ ለሚቀረው ተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል፡፡
ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የፈለገበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው አንድ ኢንስፔክተር፣ አንድ ምክትል ኢንስፔክተር፣ አንድ ምክትል ሳጂንና አንድ ኮንስታብል ግጭትና ብጥብጥ ከፈጠሩት ጋር በመተባበር ፀጥታ ለማስከበር በወጡ የሥራ ባልደረቦቻቸውና ሌሎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውን መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጎጂዎቹ በጥቁር አንበሳና በፖሊስ ሆስፒታል ኮማ ውስጥ ስለሆኑ በመሆናቸው ቃል አለመቀበሉን ገልጿል፡፡ ተጎጂዎቹን አሁን ባሉበት ሁኔታ ማናገርና ቃል መቀበል ባለመቻሉ፣ በቀጣይ የሚሻላቸው ከሆነ የእነሱን ቃል ለመቀበልና ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል የመቀበል ሥራ እንደሚቀረው ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡
ሌሎች በግጭቱና ብጥብጡ የተሳተፉና የሚይዛቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉት ፖሊስ አስረድቶ፣ በሆስፒታል ውስጥ በሞትና በሕይወት መካከል ያሉት ተጎጂዎች ሁኔታ ሳይለይለት ለተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ሊፈቀድ እንደማይገባ አመልክቷል፡፡
የተጎዱት ሰዎች ቢሞቱ ተጠርጣሪዎቹ የሚቀርብባቸው ክስ የመግደል ወንጀል ክስ ሊሆን ስለሚችል፣ በወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 63 መሠረት ዋስትና ሊከለከሉ እንደሚችሉ መርማሪ ፖሊስ በመጠቆም የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡
በግጭቱ ወቅት አንድ ተጠርጣሪ ሆዱ አካባቢ በጥይት ተመትቶ የነበረ ሲሆን፣ ቀዶ ሕክምና የተደረገለት ቢሆንም ጥይቱ ከሆዱ ሊወጣ ባይችልም፣ በወቅቱ በግጭቱ በነበረው ተሳትፎ ምክንያት ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡ ግለሰቡ በጥይት እንዴት ሊመታ እንደቻለና ማን እንደመታው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናግሯል፡፡ የአዲስ ጉዳይ ፎቶ ጋዜጠኛ አዚዛ መሐመድና የሰማያዊ ፓርቲ አባል ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ከተጠየቀባቸው ተጠርጣሪዎች መካከል ናቸው፡፡ ፖሊስ ስለነሱ የወንጀል ተሳትፎ ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ፣ በግጭቱ ወቅት ሕዝቡ ሲሸሽ ‹‹ወንድ ሆነህ የት ነው የምትሸሸው?›› በማለትና ወደ ግጭቱ እንዲመለሱ በማድረግ፣ ግጭቱን ሲያባብሱ እንደነበር የሚያሳይ በቪዲዮ የተደገፈ ማስረጃ እንዳለው በማስረዳት ዋስትናቸውን ተቃውሟል፡፡ እነሱ አደፋፍረው ባባባሱት ግጭት የተጎዱና በሆስፒታል ኮማ ውስጥ ያሉ ተጎጂዎች ጉዳይ እልባት ሳያገኝ ዋስትና እንዳይፈቀድላቸው ፖሊስ አመልክቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ፖሊስ ሆስፒታል፣ ተጎጂዎቹ ያሉበትን ደረጃ የሚገልጽ ማስረጃ እንዲልኩ በችሎት በመንገርና ፖሊስ ቀረኝ የሚለውን ምርመራ በአጭር ቀናት እንዲያጠናቅቅ በማዘዝ ለሐምሌ 29 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ፡ ሪፖርተር ጋዜጣ የኦገስት 3 ዕትም
No comments:
Post a Comment