Friday, August 8, 2014

አብርሃ ደስታ በማዕከላዊ ድብደባ እንደደረሰበትና ጨለማ ክፍል ውስጥ መታሰሩን ተናገረ 

በሃይል በማያምነው ጉዳይ እንዲፈርም መገደዱንም አስታውቋል
በሶሻል ሚዲያ ሀሳቡን በመግለጽና ስርዓቱ በትግራይ ክልል የሚፈጽማቸውን በደሎች በማጋለጥ ተለይቶ የሚታወቀው የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አብርሃ ደስታ ዛሬ አራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፌደራል ፖሊሶች ታጅቦና እጆቹ በካቴና ታስረው ሲገባ ግቢው ውስጥ ይጠባበቁት የነበሩ ሰዎች በጭብጨባ ተቀብለውታል፡፡
የአብርሃ ችሎት ለጋዜጠኞችና ለወዳጆቹ ዝግ በመሆኑ ማንም ወደ ውስጥ እንዲገባ ባይፈቀድለትም ጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጉ አብርሃ በማዕከላዊ ድብደባ እንደደረሰበትና ጨለማ ክፍል ውስጥ መታሰሩን እንዳስረዳ ተናግረዋል፡፡ከውጪ ሰዎች ጋር ትገናኛለህ የሚሉ የምርመራ ጥያቄዎች ሲቀርቡለት መቆየቱንና በማያምንበትና ባላደረገው ነገር አድርጌያለሁ በማለት እንዲፈርም መደረጉንም ለችሎቱ ማስታወቁን ጠበቃው ይፋ አድርገዋል፡፡
አብርሃን ያቀረቡት ፖሊስ የተባለውን ነገር አለመፈጸሙን በመግለጽ ተቃውሞ ማሰማታቸውንም ጠበቃው ጠቅሰዋል፡፡አብርሃ በድጋሚ የ28 ቀን ቀጠሮ ተጠይቆበት እጆቹ እንደታሰሩ ግቢውን ሲለቅ አድናቂዎቹ በጭብጨባና ከጎንህ ነን ከሚል መልእክት ጋር ሸኝተውታል፡፡

Dawit Solomon


No comments:

Post a Comment