Monday, August 4, 2014

የጦማሪያኑና ጋዜጠኞቹ የክስ መቃወሚያ ቀጠሮ ተላለፈ

የዞን ዘጠኝ ስድስት ጦማርያንና ሶሰት ጋዜጠኞች በወንጀለኛ መቅጫ ህግና በፀረ ሽብር አዋጁ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም አቅደዋል፣ ተዘጋጅተዋል፣ አሲረዋል፣ አነሳስተዋል እንዲሁም ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሁከትና በአመፅ ለመለወጥ አስበዋል ተብለው በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በህገ መንግሥትና በህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ በሚደረግ የሙከራ ወንጀል ተከሰው ባለፈው ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ከሦስት ወራት የምርመራ ጊዜ በኃላ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች በፅሑፍ የቀረበላቸውን ክስ ካደመጡ በኃላ በአቃቢ ህግና በጠበቆቻቸው መካከል በተደረገ የዋስትና ጥያቄ ክርክር ብይን ለመስጠትና የክስ መቃወሚያ ለማዳመጥ ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም የጊዜ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በዛሬው ቀጠሮ ዘጠኙም ተከሳሾች ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም በዋስትና መብት ጉዳይ በጠበቃና በአቃቢ ሕግ መካከል የተደረገው ክርክር የህግ ትርጓሜ እንደሚያስፈልገው ጠበቃዎች በጠየቁት መሰረት ከመቅረጸ ድምጹ ላይ ተገልብጦ ለህግ አስተርጓሚ እንዲላክ እንዲሁም በሌለችበት ክስ የተመሰረተባት 1ኛ ተከሳሽ ሶሊያና ሽመልስ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላት የተሰጠው ትዕዛዝ ባለመፈፀሙ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ባለፈው ቀጠሮ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ከፍርድ ቤቱ ብይን ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በዛሬው ቀጠሮ የሰጣቸው ትዕዛዞች ተፈጻሚ ባለመሆናቸው ለብይን ያስቸግረናል በሚል የክስ መቃወሚያቸውን ሳያደምጥ ቀርቷል፡፡
ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት አስተያየት በመጀመሪያው የፍርድ ቤት ውሎ ለዛሬ ቀጠሮ የክስ መቃወሚያ እንዲቀርብ ብይን የተሰጠ መሆኑን አስታውሰው ፍርድ ቤቱም ሆነ አቃቢ ህጉ የክስ መቃመወሚውን ለማየት በቂ ጊዜ የሚሰጥ በመሆኑ የክስ መቃወሚያ በጽሁፍ እንድናቀርብ ይፈቀድልን ብለው ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱም የጠበቆችን ጥያቄ በመቀበሉ የክስ መቃወሚያው ለአቃቢ ህግና ለፍርድ ቤቱ በጽሁፍ ቀርቦ በቀጣዩ ቀጠሮ በንባብ እንዲሰማ አዟል።
በ1ኛ ክስ ላይ ለተዘረዘሩ የወንጀል ድርጊቶች 5 መቃወሚያ እንዲሁም በ2ኛ ክስ ለቀረቡት የወንጀል ድርጊቶች 4 መቃወሚያ ነጥቦች የተዘረዘረበት ሰነድ “የቀረበው ክስ ከተጠቀሰው የህግ አነጋገር ጋር የሚቀራረብ አለመሆኑን፣ ተከሳሾች ፈጽመዋቸዋል የተባሉት በክስ ዝርዝሩ የተመለከቱ ተግባራት በህግ የተፈቀዱና ሕገ መንግስታዊ ጥበቃም የተደረገባቸው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መሆናቸውን፣ የቀረበው ክስ ግልፅ አለመሆኑን፣ ወስደዋል የተባሉት ሥልጠናዎችና ለመገናኛ ብዙኃን ያስተላለፉት መረጃ ወንጀል አለመሆኑን የተመለከቱ መቃወሚያዎችን የያዘ ነው፡፡
በ2ኛ ክስ የቀረበው የክስ መቃወሚያ ደግሞ ጠበቃው ማሰብ የማያስከስስና የማያስቀጣ መሆኑን፣ መደራጀት፣ የሥራ ክፍፍል መፍጠር እና የተለያዩ ሥልጠናዎችን መውሰድ ወንጀል አለመሆኑን፣ በአንድ ድርጊት ሁለት ክስ መቅረቡ አግባብ አለመሆኑ፣ የቀረበው የማስረጃ ሰነድ አለመሟላትን በተመለከተ ከወንጀለኛ መቅጫ እና ከጸረሽብር አዋጁ አንቀጽ ጠቅሰው ተቃውሞዎቻቸውን በጽሑፍ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
የዕለቱን ችሎት የሚመሩት ዳኛ ባስተላለፉት ውሳኔ የዋስትና መብት ጥያቄ ክርክር ከመቅረጸ ድምጽ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ ለህግ አውጪ አካል እንዲልክ እንዲሁም ለ1ኛ ተከሳሽ በፕሬስ ጥሪ እንዲደረግና የክስ መቃወሚያ በንባብ እንዲደመጥ ትዕዛዝ አስተላልፈው ለነሐሴ 14 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡


No comments:

Post a Comment