Wednesday, August 27, 2014

ሀገሬን ትቸ የትም አልሰደድም!! አንዱአለም አራጌ

Gashaw Mersha
ዛሬ ጧት ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ታላቁን የነጻነት ታጋይ አንዱአለም አራጌን፤ብዕሩ የማይነጥፈውን የፖለቲካ ተንታኝ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለመጠዬቅ ወደ ቃሊቲ ማጎሪያ ቤት (እነሱ ማረሚያ ቤት ይሉታል(በነገራችን ላይ እስክንድር ምኑ እንደሚታረም አይገባኝም)) ተጉዘን ነበር፡፡ ልብስ ለማስወለቅ ምንም የማይቀረውን ፍተሻ አልፈን ወደ ውስጥ ዘለቅን፡፡ ከውጭ ሲያዩት የሲኦልን ሽንቁር የመሰለው ማረሚያ ቤት ጋር ስንደርስ እስክንድር ነጋ በምትሃታዊው ፈገግታው በጥቁር ኮፍያ ታጂቦ ጠበቀን፡፡ አንዱአለም የተደራረበ ቱታ አድርጎ ከእንቅልፉ ተነስቶ የመጣ ይመስል ነበር፡፡ እስክንድር በውብ ፈገግታው ደምቆ ‹‹እስክንድር እባላለሁ›› ብሎ ሲጨብጠኝ እልህ የተቀላቀለበት ሳቅ ሳቅኩ፡፡ ኧረ አውቅሃለሁ አልኩት በትህትና፡፡ እንዴት ብዬ እስክንድርን አለማወቅ እችላለሁ፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠን ወደ አንዱአለም ዞርን፡፡ የፋክት መጽሄት አምደኞቹ ሙሉነህና ዳዊት እስክንድር ጋር በጋዜጠኛ ቋንቋ ማውራት ሲጀምሩ እኔና ጓደኞቸ በፖለቲከኛ ቋንቋ አንዱአለም ጋር ማውራት ጀመርን፡፡ ስለ ሰሞኑ የጋዜጠኞች ስደት፤ስላለው የፖለቲካ ትኩሳት እንደ አቅሚቲ አወራነው አንዱአለምን፡፡ ስለ ስደት ስናወራ አንዱአለም እንዲህ ሲል በኩራት ነገረን፡፡ ‹‹እኔ ሀገሬን ለቅቄ የትም አልሰደድም፤ መሞት ካብኝም ከእውነቴና እምነቴ ጋር እዚሁ እሞታለሁ›› አለን፡፡ ስደት መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል አጽንኦት ሰጥቶ ተረከልን፡፡ ‹‹እኔ ወደ አንድነት ስመጣ ሊያስሩኝ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነበርኩ›› ይላል አንዱአለም፡፡ ራስ ወዳድነት እስካልጠፋ ድረስ ለውጥ ማምጣት ከባድ ነው ሲል ስለሚከፈለው መስዋዕትነት ተረከልን፡፡ ልጆቹንና አፍላ ትዳሩን ትቶ ለእድሜ ልክ እስራት የተዳረገው አንዱአለም ምንም የጸጸት ስሜት
አይሰማውም፡፡ ‹‹ያለ መስዋትነት ስርዬት የለም፡፡ መሰደድ ተሸናፊነት ነው›› እያለ በጣፋጭ አንደበቱ ለትግል እንበረታ ዘንድ ወተወተን፡፡ ለእያዳንዳቸው አንዳንድ ጆሮ ጠቢ ይሁኑ ጥበቃ ምናቸው የማይታወቅ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች ከአጠገባችን ቁመዋል፡፡ እነዚህ ጥበቃዎች የመቆማቸው ሚስጥር በነጻነት ለማውራት ራሳችን እናቅብ ዘንድ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ታሳሪዎቹም ሆነ ጠያቂዎቹ ነጻ ሰዎች ስለሆንን ለጆሮ ጠቢ ልንደነግጥ አንችልም፡፡
በዚህ ጣፋጭ ውይይት መካከል ከሰማይ ቤት ታዞ የመጣ ደንቃራ ዝናብ የጣራውን ቆርቆሮ ይነርተው ጀመር፡፡ የጣራው መንኳኳት አላሰማማን አለ፡፡ ፊት ለፊት እዬተያየን በእጅ እንቅስቃሴ በታጀበ አነጋገር እዬጮህን አወራን፡፡ በመካከል የተፈቀደችልን ግማሽ ሰዓት እንደተገባደደች ጥበቃወቹ ነገሩን፡፡ ልንሰናበት ነው፡፡ አንበሳዎቹ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በሰንካላ ምክንያት ከብረት አጥሩ ማዶ ሊዘጋባቸው መሆኑን ሳስብ ሀገሬ አስጠላችኝ፡፡ ለመንግስት አሸባሪዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ የነጻነት ታጋዮች የሆኑት መሲሆች በጠባብ በረት ሊወሰኑ ነው፡፡ ሀገሬ ወርቅ ለሰጣት ድንጋይ፤ዳቦ ለጠዬቃት እባብ ስትሰጥ የምትኖር አሮጊት እናት ናት፡፡ እየተነፋፈቅንም ቢሆን የግዳችን ቻው አልናቸው፡፡ ፈገግታቸው ወደ አዕምሮዬ ዘልቆ ገባ፡፡ ምን አይነት ጥንካሬ ነው ታስሮ እንኳ የማይሟሽሽ ስል አሰብኩ፡፡ የእውነት ኮራሁባቸው!! ማህተማ ጋንዲ፤ኒሰር ማንዴላ፤አብርሀም ሊንከን እያልኩ የነጻነት ታጋዮችን ስም ባህር ተሻግሬ አልጠራም፡፡ ጦቢያ ያፈራቻቸው ጀግኖች እስክንድር ነጋ እና አንዱአለም አራጌ እስከ ዘላለም በልቤ ማህደር ላይ ታትመዋልና፡፡ ጀግኖቸ በደም ስሬ ሲዟዟሩ ይሰማኛል፡፡ ልቤን ቃሊቲ ትቸ በድን አካሌን እዬጎተትኩ በፍርሃት ወደ ታፈነችው ቤቴ ተመለስኩ፡፡
ሀገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡


No comments:

Post a Comment