(ኢ.ኤም.ኤፍ) ሰሞኑን በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ማዋከብ ተከትሎ በርካታ ጋዜጠኞች ከአገር መውጣታቸው ይታወሳል። በተለይም ገዢው አካል በአምስት የፕሬስ ውጤቶች፣ ሎሚ፣ አፍሮ ታይምስ፣ እንቁ፣ አዲስ ጉዳይና ጃኖ ፕሬሶች ላይ ግልጽ የሆነ ህገ ወጥ ጥቃት እያደረሰባቸው በመሆኑ አስራ አንድ ጋዜጠኞች አገር ለቀው ለመሰደድ በቅተዋል። አሁን ደግሞ ሌላኛው እና 12ኛው ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ከአገር ለመውጣት መገደዱን በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ ከላከው መረጃ ለማወቅ ችለናል።
ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን በተለይ በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ይደረጉ የነበሩ ሰላማዊ ሰልፎችን በመከታተል የጽሁፍ እና የፎቶ ዘገባ በማቅረብ የሚታወቅ ጋዜጠኛ ነው። ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ባለፈው እሁድ አትላንታ ከሚገኘው ማህደረ አንድነት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ “በቀጣይ እርምጃ ሊወስዱብኝ እንደሚችሉ መረጃ ስለደረሰኝ ከአገር ለመውጣት ተገድጃለሁ።” በማለት ገልጿል። (ሙሉውን ቃለ ምልልስ እንደደረሰን እናቀርባለን)
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማዋከብ፣ በማሰር እና ለስደት በመዳረግ ከአለም አስር መጥፎ አገሮች ተርታ የተመደበች መሆኗን የሲ.ፒ.ጄ እና ሌሎች የፕሬስ ተቋማት ደጋግመው ይገልጻሉ።
ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞንን በቀጥታ በማግኘት መርዳት ለምትፈልጉ የኢሜይል አድራሻው dawit341@gmail.com መሆኑን በዚህ አጋጣሚ እናሳውቃለን።
No comments:
Post a Comment