ሄኖክ የሺጥላ
በምዕራብ አፍሪካ የተነሳውን የኢቦላ ቫይረስ ተከትሎ የተለያዩ ሃገራት ወረርሽኙ ወደታየባቸው ሀጋሮች የሚያደርጉትን ማንኛውም አይነት የአየርም ሆነ የየብስ፣ የንግድና የቱሪዝም ፣ የትምህርትና የስልጠና እና ሌሎችንም አይነት የንግድ ይሁን መሰል ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አቁመዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ግን ፣ አይዞዋችሁ ፣ ወደተባለው አደገኛ መንደር መሄዱ አይደልም መፈራት ያለበት ፣ መፈራት ያለበት ቦሌ ላይ የምናደርገው የቁጥጥር ስርዓት ነው ፣ በዚህ ደሞ ሃሳብ አይግባችሁ እኛ እንኩዋን ኢቦላን አንዳርጋቸው ጽጌንም ቢሆን ይዘናል እያሉን ያሉ ይመስላሉ። አክለውም እንደው ባጋጣሚ ይሄ ኢቦላ የተባለው ቫይረስ ቢገኝ እንኩዋ ባ’ስር አልጋና በሃያ ዶክተሮች ታጥቀን እየጠበቅነው ነው እያሉ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት “The World Health Organization (WHO)” ቫይረሱ ሊያመጣ የሚችለውን እልቂት እየተናገረ ፣ በይበልጥም የህክምና ጠበበብቶች በአማካይ ለ 21 ቀናት ቫይረሱ ምንም አይነት የበሽታ ምልክት ሳያሳይ በተጠቂው ግለሰብ ላይ የመቆየት እቅም እንዳለው እየተናገሩ፣ የኛ ጠቦቶች ( ማለቴ ጠበብቶች ) ግን ተጠቂውን ( ወይም ለነሱ ታጣቂውን ) የምንለይበት ልዩ ዘዴ ስላለ አትቸገሩ እያሉን ነው።
እኔ እምለው ኢቦላም ላይ ከፍተኛ ክትትል ለማድረግ በሽታው ከዔርትራ መነሳት ነበረበት ማለት ነው? መንግሥቴ ምነው ያልተጠመደ ቦንብ ከምታፈነዳብን ምናለ ይቺን ኢቦላ ከመፈንዳቱዋ በፊት ብታክሽፍልን ? ወይስ የምርጫ ታዛቢዎች ወደ ሀገሪቱዋ እንዳይገቡ ለማድረግ እየተዶለተ ያለ ነገር አለ? መቼም እናንተ እኮ ስለ ሰው ሕይወት ያላችሁ ግንዛቤ ጅብ ስለ አህያ ስጋ ያለውን ያህል ግንዛቤ እንደማይሆን እጠረጥራለሁ ። እኔን የገረመኝ ግን እነዚያ 20 ዶክተሮች እነማን ይሆኑ ? ምናልባት ስርዓቱን በመቃወማቸው የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ምስኪኖች?
ለማንኛውም ኢቦላ ክላሽንኮቭ ተሸክሞ ፣ ቦምብ ታጥቆ ፣ በጾረና በኩል የሚመጣ ዋርድያ ወይም ጀሌ ወይም ማንጁስ አይደለም ፣ የኢቦላን ምንነት ለመረዳት ቢያንስ ሚንስትሪን ማለፍ የግድ ይላል ። በአምስተኛ ክፍል እውቀት ግን እንኩዋን ኢቦላን የሆድ ድርቀትን መረዳት የሚከብድ ይመስለኛል ። ለናንተ አይነቱ ድፍን መሀይም የዚህ በሽታ ጥፋት እና ክፋት ሊታያችሁ ያልቻለው ደሞ ነገሮችን ሁሉ የምታዩት የታንክ ሰንሰለት ባያችሁበት አይናችሁ ስለሆነ ነው ። ህዝቡ ግን ዝም ብሎ እንደሚታረድ በግ የሆነ ይመስለኛል ። ማን ያውቃል መጥፍያችሁስ ቢሆን?
No comments:
Post a Comment