ኢሳት ዜና :-የምስራቅ አፍሪካ የሰብአዊ መብቶች ሊግ ለኢሳት በላከው መግለጫ ካለፉት 2 ሳምንታት ጀምሮ በተለያዩዩኒቨርስቲዎች የተጀመረውን የፖለቲካ ስልጠና ተከትሎ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ከ100 በላይ እንዲሁም ከወለጋ የኑቨርስቲ 5 ተማሪዎች ታፍነው ተወስደዋል። የፖለቲካ ስልጠናው አጀንዳ የአገር አንድነት የሚል አላማ ቢኖረውም ፣ በተግባር እየታየ ያለው ግን ተማሪዎችን እየለዩ ማሰር ነው ነው ብሎአል።
ከአምቦ ዩኒቨርስቲ የተያዙ ተማሪዎች ሰንቀሌ እየተባለ ወደ ሚጠራ እስር ቤት ተወስደዋል። ተማሪዎቹ ስለ አገር አንድነት ከመነጋጋር በፊት በቅርቡ ጓደኞቻቸውን የገደሉ ፖሊሶች ለፍርድ እንዲቀርቡ በመጠየቃቸው መታሰራቸውን ድርጅቱ አስታውቋል። ከአራት ቀናት በፊት ደግሞ 5 የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች 4866 ኢቲ የሚል ታርጋ ባለው መኪና ተጭነው መወሰዳቸውንና እስካሁን ድረስ ያሉበት ቦታ አለመታወቁን የሰብአዊ መብት ሊጉ ገልጿል። በኢሉ አባቦር ዞን ፣ በዶራኒ ወረዳ ፣ ኢሊሞ ቀበሌ ደግሞ ከ10 ቀናት በፊት ከ100 በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ገልጾ፣ ዋቅቶላ ጋርቤ፣ ሲሳይ አማና፣ ቲኪ ሱፋ፣ ኢታና ዳጋፋ፣ ባድሩ ባሻ ፣ ከማል ዛሊ፣ ራሺድ አብዱ ፣ ዘትኑ ዋቆ፣ ዳጋፊ ቶሊ፣ አዳም ሊቂዲ፣ ኢንዱሽ መንግስቱ፣ ዲቢሳ ሊባንና ኦፍታ ጂፋር የተባሉት ነዋሪዎች በኢሊሞ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ ብሎአል።
ባለፈው ሚያዚያና ግንቦት ወር በክልሉ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ በሽዎች ከታሰሩት መካከል ከ100 በላይ የሚሆኑት በአካባቢ ፍርድ ቤቶች እንዲፈቱ ውሳኔ የተላለፈ ቢሆንም፣ የመንግስት ባለስልጣኖች ጣልቃ በመግባት እንዳይፈቱ ማድረጋቸውን የገለጸው ሊጉ፣ በደምቢ ዶሎ 64 ፣ በአምቦ 10፣ በሲቡ ሲሪ እና ዲጋ ወረዳዎች ደግሞ 40 እስረኞች እንዲፈቱ ትእዛዝ ቢተላለፍም ፣ የወረዳ ባለስልጣኖች ውሳኔውን ሽረውታል። አንዳንዶች ከፌደራል በመጡ ባለስልጣናት ከ6 እስከ 10 አመታት የሚቆይ ፍርድ እንደተፈረደባቸው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ለእስረኞች ጥብቅና የቆሙ ጠበቆች ማስፈራሪያ እንደደረሳቸው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጽመውን ከፍተኛ የሰበአዊ መብት ጥሰት እንዲያቆም አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶችና መንግስታት ጫና እንዲያደርጉ በመግለጫው አመልክቷል። በታሰሩት ዙሪያ መንግስት የሰጠው መግለጫ የለም።
No comments:
Post a Comment