ለበርካታ ዓመታት ታጥረው በተቀመጡ ቦታዎች ወቀሳ ቀረበ
የአዲስ አበባ ከተማን የመሬት ማኔጅመንት አሠራር ማስተካከል የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ቢባልም፣ የሊዝ አቀፍ ከወጣበት ከኅዳር 2004 ዓ.ም. በኋላም በርካታ ቦታዎች በሕገወጥ ወራሪዎች መያዛቸውን አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡
‹‹የመሬት ወረራ የሚባል ካንሰር አለቀቀንም፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ ኩማ ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ እስካለፈው ዓርብ ድረስ በዘለቀው የአስተዳዳሩ የ2006 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡
የማስፋፊያ አካባቢዎች ከሆኑት ስድስት ክፍላተ ከተሞች የመጡ የወረዳ አመራሮች የመሬት ወረራው ቀላል በማይባል ደረጃ መኖሩን አምነው፣ ለዚህም የወረዳ አመራሮችና ፈጻሚ አካላት አድርባይነት የሚያጠቃቸው በመሆኑና ነገሮችን አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ለተከሰቱት ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተለይ በኮልፌ ቀራኒዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በአቃቂ ቃሊቲና በየካ ክፍላተ ከተሞች የመሬት ወረራው በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ንብረትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሐረጐት ዓለሙ በስብሰባው ላይ እንደገለጹት፣ የመሬት ወረራ በከፍተኛ ደረጃ እየተካሄደ ቢሆንም በክፍለ ከተማና በወረዳ የሚገኙ አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ዕርምጃ አይወስዱም፡፡
አቶ ሐረጐት እንዳሉት፣ በ2004 ዓ.ም. በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 1,400 ሕገወጥ ቤቶች ፈርሰው ነበር፡፡ ነገር ግን የፈረሱት ቤቶች በድጋሚ ተሠርተዋል፡፡ ‹‹በዚያው ክፍለ ከተማ 100 ሔክታር መሬት ለኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ መስጠት ቢኖርብንም፣ በቦታው ላይ ሕገወጥ መሬት ወራሪዎች ቤት ገንብተውበታል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ሐረጐት ጨምረው እንደገለጹት፣ የሊዝ ሕጉ በሕገወጥ የመሬት ወራሪዎች ላይ እስራትና የገንዘብ ቅጣት የሚጥል ቢሆንም ዕርምጃ በመወሰድ በኩል ግን አመራሮች የጀመሩት ተግባር የለም፡፡
‹‹ከክፍላተ ከተማና ከወረዳዎች ጋር በፍፁም አልተግባባንም፤›› በማለት አቶ ሐረጐት የችግሩን ሥር መስደድ አስገንዝበዋል፡፡ በስብሰባም ላይ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለበርካታ ዓመታት ያለሥራ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችና በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ችግር መኖሩ ተነስቷል፡፡
የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኃይሌ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች ለበርካታ ዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ አለመውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በሕጉ እንደተቀመጠው ወረዳዎች ሁለት ፎቅ ድረስ ላሉ ግንባታዎች የግንባታ ፈቃድ መስጠት ይችላሉ፡፡ ክፍላተ ከተሞች ደግሞ እስከ አምስት ፎቅ ድረስ የግንባታ ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ በማዕከል ደግሞ ከስድስት ፎቅ በላይ ለሆኑ ግንባታዎች የግንባታ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ሦስቱም ተዋረዶች የግንባታ ፈቃድ ሲሰጡ በውል የታሰረ ቢሆንም፣ ግንባታ በሚያዘገዩ አልሚዎች ላይ ግን ዕርምጃ እንደማይወሰድ አቶ ሰለሞን ወረዳዎችና ክፍላተ ከተሞች ላይ ጣት ቀስረው ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የወረዳና የክፍላተ ከተማ አመራሮች ግን የአቶ ሰለሞንን ወቀሳ አይቀበሉትም፡፡ ምክንያታቸውን ሲያስረዱም በማዕከል ደረጃ የተሰጡ ነገር ግን ለበርካታ ዓመታት ያለግንባታ የተቀመጡ ቦታዎች ላይ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዕርምጃ አለመውሰዱን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ግንባታ ሳይካሄድባቸው ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ቦታዎች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ለቢሮውና ለካቢኔው የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ካቢኔውም ሆነ የመሬት ቢሮው ውሳኔ አለመስጠቱን ይናገራሉ፡፡
የመሬት ቢሮው የራሱን ሥራ በአግባቡ ሳይሠራ ወቀሳ መሰንዘሩ አግባብ አለመሆኑን አመራሮች ጠቅሰው፣ ዕርምጃ በመውሰድና ባለመውሰድ በኩል ከፍተኛ የሙስና ዝንባሌ እንዳለና ዕርምጃ ይወሰድ ሲባል ደግሞ በኔትወርክ የታገዘ ከፍተኛ ግምገማ ተደርጐ ውሳኔ ሰጪው ከጨዋታ ውጪ እንዲወጣ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ሌላው የተነሳው ችግር የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ነው፡፡ በርካታ ባለይዞታዎች የዕድሳት ፈቃድ ወስደው ራሱን የቻለ ሌላ ሕገወጥ ግንባታ እንደሚያካሂዱ ተገልጿል፡፡ ይህንን ተግባር አመራሩ በአድርባይነት የሚያካሂደው ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ሕገወጦች እየተጋለጡ ያሉት ደስተኛ ያልሆነ አካል ቅሬታ ሲያቀርብ ብቻ እንጂ የአሠራር ሥርዓቱ እያጋለጣቸው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
ለምሳሌ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ 95 ፈጻሚዎችና ስምንት አመራሮች ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ እገዳ ድረስ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸውና ዕርምጃ ሊወሰድባቸው የቻለውም ቅሬታ ቀርቦባቸው ማጣራት ከተካሄደ በኋላ እንደሆነ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
ሳምንቱን ሙሉ በተካሄደው የአዲስ አበባ አስተዳደር የ2006 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ግምገማ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቢሮዎች እንዲሁም፣ አሥሩ ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎች ተገምግመዋል፡፡ ግምገማውን የመሩት ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውና የአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን ናቸው፡፡
No comments:
Post a Comment