“በእኛ እምነት ታሪክ ከነባራዊ ሁኔታ ዉጭ በምኞትና በዘፈቀደ አይሰራም። የሚሰራ ቢሆን ኖሮ ነገስታቱና አምባገነኖቹ ዘሬም በዙፋናቸዉ ላይ በተገኙ ነበር። ባለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝቦች መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆመዉ ከዚህ ወዴት እንደሚሄዱ ግልጽ ኢየባልሆነበት ሰዐት ሥልጣን ላይ ያለዉም ሆነ የሌለዉም የግሉን የተስፋ ጎዳናን እዉነተኛዉ የወደፊት ጎዳና አድርጎ የሚያይ ከሆነ ዛሬም እንደ ትናንቱ ከታሪክ መማር አልቻልንም ማለት ነዉ”።“ከዲሞክራሲ ጋር ሲወዳደር ፍትህ ለሚለዉ ጽንሰ ሀሳብ “ኢትዮጵያዊኛ” ቃላቶች ያሉን መሆኑ የሚያስረግጠዉ ነገር ቢኖር ፍትህ ከማንነታችን ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነዉ። ኢትዮጵያዉያን ፍትህ ሲጓደል “በህግ አምላክ” ብለዉ በዳያቸዉን ለማስቆም የሚያሰሙት ጩኸት ፍትህ ከፈጣሪያቸዉ የተሰጠ ከሰብዓዊነታቸዉ ተነጥሎ የማይታይ እሴት አድርገዉ እንደሚመለከቱት የሚያመለክት ነዉ። በምድር ላይም ፍትህ የሚሰጥ ዳኛ ጠፍቷል ብለዉ ሲያስቡ እጃቸዉን ወደ ፈጣሪያቸዉ ዘርግተዉ አንተዉ ፍርዱን ስጠና የሚሉት ከፈጣሪያቸዉ ፍጹምነት የሚመነጭ እዉነተኛ ዳኝነት አለ ብለዉ ስለሚያምኑ ነዉ። ከዚህ በላይ ባጭሩ የተባለዉ የሚጠቁመዉ በኢትዮጵያዉያን ባህልና ስነ ልቦና ዉስጥ የፍትህ ጽንሰ ሀሳብ ያለዉን ትልቅ ትርጉምና ቦታ ነዉ”።የታሪክን ነባራዊነት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍትህ የሚሰጠዉን ከፍተኛ ቦታና ለነጻነት ያለዉን አመለካከት በተመለከተ ከዚህ በላይ ያሰማናችሁን ሁለት አዉዶች በሁለት የተለያዩ መጽሐፎቹ ዉስጥ የጻፈዉ ዛሬ ፍትህ አልባ በሆነዉ የወያኔ ስርዐት ዉስጥ ለፍትህ፤ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ሲል ለፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ያለዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ነዉ። አዎ የፍትህና የነጻነት አርበኛዉ አንዳርጋቸዉ በግልጽ አንዳስቀመጠዉ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ፍትህ እስከነ ስሙ ሙልጭ ብሎ በመጥፋቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለት እጆቹን ወደ ሰማይ ዘርግቶ እባክህ አምላኬ “ወይ ዉረድ ወይ ፍረድ” እያለ ፈጠሪዉን እየተማጸነ ነዉ። በእርግጥም ፍትህ ፈጣሪያችን ያደለን ትልቅ ማህበራዊ እሴት ነዉ፤ ሆኖም ይህንን
የፈጣሪ ስጦታ እኛን የመሰሉ ሌሎች ሰዎች መጥዉ ሲቀሙንና እንዳሰኛቸዉ ሰረግጡን አንረገጥም ብለን እራሳችንን ነጻ ማዉጣትና የተቀማነዉን ፍትህ ከወያኔ ዘረኞች ቀምተን መልሰን ማህበራዊ እሴት የማድረጉ ኃላፊነት የእኛ የራሳችን ነዉ እንጂ የፈጣሪ አይደለም። ፈጣሪያችን ፍትህና ነጻነትን አንዴ ሰጥቶናል እነዚህን የፈጣሪ ስጦታዎች እንዳንቀማ መጠበቅና ከተቀማን ደግሞ ታግለን ማስመለስ ያለብን እኛ ብቻ ነን።አንዳርጋቸዉ ጽጌ የአማራዉ ህዝብ ከየት ወዴትበ1966 ዓም ጩኸታችን በሙሉ የፊዉዳሉ ስርዐት እንዲፈርስ ነበር እንጂ የምናፈርሰዉ ስርዐት በምን ይተካል ለሚለዉ ጥያቄ መልስ ስላልነበረን በወቅቱ በስራዉ ጠባይ የተነሳ ተደራጅቶ የነበረዉ የወታደሩ ክፍል ስልጣን ተረክቦ አገራችን 17 አመት ሙሉ የደም ባህር ዉስጥ እንድትዋኝ አድርጓታል። የደርግን ስርዐት ለማፍረስ በተደረገዉ ትግል ዉስጥም ከ1966ቱ ስህተታችን ምንም ባለመማራችን መሳሪያ ከታጠቀ ኃይል ሁሉ ጋር ጉሮ ወሸባዬ መዝፈን ጀመርን። ደርግን የሚዋጉ ኃይሎች ሁሉ የህዝብና የአገር ወዳጆች እየመሰሉን በየጫካዉ እየሄድን ተቀላቅለናቸዉና ዛሬ ይሄዉና እኛዉ እራሳችን ያጠናከርናቸዉ ኃይሎች ስልጣን ይዘዉ ካፈረሱት ስርዐት በከፋ መልኩ አገርንም ህዝብንም እያፈረሱ ነዉ። ደርግ ከፊዳሉ ስርዐት ዉድቀት ምንም ባለመማሩ ሃያ አመት ሳይሞላዉ እሱም እንደ ፊዉዳሉ ስርዐት የታሪክ ቆሻሻ ዉስጥ ተጥሏል። ከፊዉዳሉም ከደርግም ስርዐት ዉድቀት መማር ያልፈለጉት የዛሬዎቹ ዘረኞች ደግሞ የማይቀረዉን ዉድቀታቸዉን እየጠበቁ ነዉ። የወያኔ ዘረኞች ከታሪክ አለመማር ካሁን በኋላ ሊገርመን ወይም ሊያጠያይቀን አይገባም፤ እነሱ ወደዱም ጠሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተምራቸዋል። ዛሬ ዋናዉ ቁም ነገር ወይም ትልቁ ጥያቄ እኛ ካለፉት ሁለት ግዙፍ ስህተቶቻችን ተምረናል ወይ የሚለዉ ጥያቄ ነዉ፡፡ ስራችን የወያኔን ስርዐት ማፍረስ ብቻ ነዉ ወይስ ከወያኔ መፍረስ በኋላስ ለሚለዉ ጥያቄ መልስ አለን። ወያኔን እያፈረስን ስንሄድ ከማፍረስ ጎን ለጎን ወያኔን የሚተካ ስርዐት እየገነባን ነዉ ወይስ ሩጫችን ሁሉ ማፍረሱ ላይ ብቻ ነዉ ያተኮረዉ።የወያኔን ስርዐት ለማፍረስ በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ የተቃዋሚ ኃይሎች መሰባሰብና በአንድነት መቆም ቁልፍ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፤ ሆኖም በእኛ እምነት እጅግ በጣም ከባዱና ዉስብስቡ ስራ ወያኔ የፈጠረዉን ዘረኛ ስርዐትና ቆሻሻ ባህል ማፈራረስና በምትኩ ሌላ መገንባት ነዉ እንጂ ወያኔን ማስወገዱ አይደለም። ወያኔ በህዝብ የተጠላና የተተፋ ስርዐት ስለሆነ በራሱ ዉስጥ በሚፈጠር ቀዉስ ወይም በአንድ እራሱን ለህዝባዊ አመጽ ባዘጋጀ ጠንካራ ድርጅት ተጠራርጎ ሊጠፋ የሚችል ድርጅት ነዉ። ለአገራችን ለኢትዮጵያ በጎ የምንመኝና ዛሬ ወያኔን በተለያየ መልኩ የምንፋለም የነጻነት ኃይሎች አጅግ በጣም ሊያሳስበን የሚገባና አገራችን ኢትዮጵያም በቀላሉ የማትወጣዉ ማጥ ዉስጥ የምትገባዉ ወያኔ ከእነዚህ ሁለት መንገዶች በአንዱ ከወደቀ ነዉ። ይህንን ታሪካዊ ጥፋት እዉን ከመሆኑ በፊት መቀየር የምንችለዉ ደግሞ ወያኔ ከወደቀ በኋላ ሳይሆን ዛሬ ለመዉደቅ ሲንገዳገድ ነዉ።አንዳርጋቸዉ አገራችን ብዙ አደጋዎች ፊቷ ላይ አንደተደቀኑባት በትክክል ካሳየን በኋላ አደጋዎቹን አንዴት መከላከል አንዳለብንም በቃላትና በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም በረሃ ዉስጥ ገብቶ መሬት ላይ እየተኛ ያሳየን የተግባር ሰዉ ነዉ። ዛሬ የወያኔ ዘረኞች አንዳርጋቸዉን አስረዉ የሚያሰቃዩት የአንዳርጋቸዉ ዕቅድና የጀመራቸዉ ስራዎች የእነሱን ቆሻሻ ስርዐት ጠራርጎ ኢትዮጵያን እንደሚያጸዳ ከወዲሁ ስለተረዱ ብቻ ነዉ። በእርግጥም አንዳርጋቸዉ የሽብርተኞች ድርጅት መሪ ቢሆን ኖሮ ጨዋዉና አርቆ አስተዋዩ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያሸብረዉ ሰዉ ሲታሰር ደስታዉን ነዉ እንጂ ቁጣዉንና ሀዘኑን አይገልጽም ነበር። የአንዳርጋቸዉ መታሰርና አንደ ማዕበል ገንፍሎ የወጣዉ ህዝባዊ ቁጣ ወለል አድርጎ ያሳየን ነገር ቢኖር አትዮጵያ ዉስጥ አሸባሪዉ ማን እንደሆነ ነዉ።ወያኔን የሚተካ ጤነኛ አካል ሳናዘጋጅ በጅምላ ወያኔ ይወገድ አንጂ ከዚያ በኋላ ያለዉ አይቸግርም የሚለዉ አባባል አደገኛ አባባል ነዉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መስማማት አቅቶን ለእነዚህ የቀን ጅቦች የምንሰጣቸዉ ግዜና በየግላችን በተናጠል የምናደርገዉ ጉዞ አገራችን ኢትዮጵያን ከድጡ ወደ ማጡ ይዟት የሚሄድ አጅግ በጣም አደገኛ ጉዞ ነዉ። “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ስንል እናት አገራችን ኢትዮጵያን ከእንደነዚህ አይነት አደጋዎች ለማዳን ምንም አይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል ማለት ነዉ።የለበስነዉ ልብስ ከመጠን በላይ ሲቆሽሽ ያለን ምርጫ የተዘጋጀ ቅያሪ ካለን እሱን ቀይረን የቆሸሸዉን ማጠብ ነዉ፤ ቅያሪ ካሌለን ግን አዲስ ልብስ መግዛት ነዉ ያለብን እንጂ መቼም ካላበድን በቀር በቆሻሻ የጀቦደ ልብስ ለብሰን አደባባይ አንወጣም። ከ1966ቱና ከ1983ቱ ታሪካዊ ስህተቶች የተማርን ኢትዮጵያዉያንም ማሰብና ማድረግ ያለብን እንደዚሁ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ስርዐት ከመጠን በላይ ቆሽሿልና በበረኪና ታጥቦ የሚጸዳ ከሆነ በፍጥነት መታጠብ አለበት፤ አለዚያም ወያኔን ከማስወገዱ ሂደት ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ አዲስ ስርዐት በጋራ መገንባት እንዳለብን ለአፍታም ቢሆን ልንዘነጋዉ የማይገባን ኢትዮጵያዊ አደራ ነዉ።ዛሬ እጁ በዘረኞች ተይዞ የሚሰቃየዉ አንዳርጋቸዉ ጽጌ የኑሮ ጓደኛዉን፤ አንድ ፍሬ ልጆቹንና ወንድሞቹን ትቶ ከሞቀዉ የአዉሮፓ ኑሮ በረሃ ወርዶ የማደራጀትና የማስተባበር ስራ መስራት የጀመረዉ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸዉን የአገራቸን ዉስብስብ ችግሮች በሚገባ ስለተገነዘበና ያለፉት ስህተቶቻቸን ላለመድገም የቆረጠ ሰዉ ስለሆነ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ከታሪክ እንማር ሲል የፍትህና የዲሞክራሲ ትግላችን አላማና ግብ ወያኔን መጣል ብቻ ሳይሆን ካሁን በኋላ በሰላምና በእኩልነት ሊያኖረን የሚችል ስርዐትም መገንባት አለብን ማለቱ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ፍትህ የምንለዉ ጽንሰ ሃሳብ ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ጋር የተቆራኘ ነዉ ሲል ይህንን ከማንነታችን ጋር የተቆራኘ ትልቅና እጅግ በጣም አስፈላጊ ማህበራዊ እሴት በዘረኞች ተቀምተን እንኳን ሃያ ሦስት አመት አንድ ምሽትስ ቢሆን እንዴት ተኝተን እናድራለን ማለቱ ነዉ። አንዳርጋቸዉ ለአገራችን አንድነትና ለዲሞክራሲ መብታችን መከበር እስከ ሞት ድረስ መሄድ አለብን ሲል ዲሞክራሲ ያልሞረደዉ አንድነት ወይም አንድነት ያልሞረደዉ ዲሞክራሲ እስካልገነባን ድረስ ትግላችን አያቆምም ማለቱ ነዉ።ዛሬ በአለም ዙሪያ በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያዉያን “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” በሚለዉ መፈክር ዙሪያ የተሰባሰቡት የአንዳርጋችዉ አላማና የአርባ አመት ጉዞ የእነሱም አላማና የወደፊት ጉዞ ነዉ ብለዉ ስለሚያምኑ ነዉ። “እኔም አንዳርጋቸዉ ነኝ” ማለት እኔም ልክ እንደ አንዳርጋቸዉ ጽጌ፤ እንደ እስክንድር ነጋ፤ ሠላማዊት ሞላ፤ በቀለ ገርባ፤ አንዱአለም አራጌና ዞን ናይን ብሎገርስ የመብት፤ የነጻነት፤ እኩልነትና የአገር አንድነት ጉዳይ ያንገበግበኛልና ለእነዚህ እሴቶች መከበር እኔም አንደነዚህ ጀግኖች ኢትዮጰያዉያን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ማለት ነዉ።በአለማዉ የሚጸና፤ ለአላማዉ ግብ መምታት የተዘጋጀና በህይወቱ የቆረጠን ሰዉ ደግሞ ከድል ወዲህ ማዶ የሚያቆመዉ ምንም ምድራዊ ኃይል የለም።ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
No comments:
Post a Comment