Wednesday, August 1, 2018

የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበርን የማካለሉ ስራ እንዲጀመር ተጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 25/2010) በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አቅራቢያ ያለውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት የድንበር ማካለሉ በአስቸኳይ እንዲጀመር ሱዳን ጠየቀች።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤል ድሬድሪ ሞሐመድ እንደገለጹት በእርሻ ቦታ ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት የሚፈጠረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት አስቸኳይ የማካለል ስራ መጀመር ይኖርበታል።
በሱዳን ወታደሮችና በኢትዮጵያ ገበሬዎች መካከል በተደጋጋሚ በሚከሰተው ግጭት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።
የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኤል ድሬድሪ ሞሐመድ በካርቱም ከኢትዮጵያ አምባሳደር ጋር ውይይት አድርገዋል።
የውይይታቸው መነሻም በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ግጭት እየተባባሰ በመምጣቱ ነው ተብሏል።
እናም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው የድንበር ማካለል ጉዳይ በአስቸኳይ መጀመር አለበት ነው ያሉት።

በሰሜን ጎንደር የሱዳን ድንበር አዋሳኝ አካባቢ በእርሻ መሬት ሳቢያ በተፈጠረ ግጭት በርካታ የአካባቢው ገበሬዎች መሞታቸው ሲነገር ቆይቷል።
በተለይ ደግሞ የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ጦሩን በማሰማራት የኢትዮጵያ ገበሬዎችን መግደሉ ብዙዎቹን ሲያስቆጣ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ገበሬዎችም ራሳቸውን ለመከላከል በወሰዱት ርምጃ በተመሳሳይ ሁኔታ የሱዳን ወታደሮችን ገድለዋል።
በድንበሩ አቅራቢያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአካባቢውን ሰላም አላስከብርም በሚል ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።
በኋላ ላይ ግን መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው በመሰማራት ርምጃ ወስዷል።
በአካባቢው ያለውን የድንበር ግጭት ለመፍታት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ወደ ካርቱም በመሄድ ጉዳዩን ለሱዳን መንግስት አንስተውም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ከሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ጋር ውይይት አድርገው የሱዳን ጦር ከአካባቢው እንዲሸሽ መጠየቃቸው ይታወሳል።
እናም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የድንበር ማካለሉ በአስቸኳይ እንዲጀመር የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment