Friday, August 3, 2018

በሶማሌ ክልል ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ጅቡቲ ተሰደዱ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 27/2010) በሶማሌ ልዩ ሃይል የሚፈጸመውን ጥቃት በመሸሽ ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ጅቡቲ መሰደዳቸው ታወቀ።

ከትላንት ጀምሮ በደወሌ፣ አይሻና ሽንሌ ዞን የተሰማራውና በአብዲ ዒሌ የሚታዘዘው ልዩ ሃይል ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ህዝቡ በመሰደድ መጀመሩ ነው የተገለጸው። በጥቃቱም የተገደሉ ሰዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል።



የፌደራል ፖሊስ ህዝቡን ከልዩ ሃይሉ ጥቃት ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በድሬዳዋ በሶማሌ ክልል የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የተዘጋጀውንና ከ1500 በላይ ሰዎች እየተሳተፉ ያሉበትን የሰላም ኮንፍረንስ ለማወክ የተደረገው ሙከራም መጨናገፉ ታውቋል። የሶማሌ ክልል ቀውስ ዳግም አገርሽቷል።

ላለፉት ሶስት ወራት ያዝ ለቀቅ እያደረገ የዘለቀው ተቃውሞ ከትላት ጀምሮ በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች ተቀስቅሶ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ለማወቅ ተችሏል። ከትላንት ጀምሮ እየተካሄደው ያለው ተቃውሞ በተለይ አይሻ በተባለች ከተማ ላይ ጠንከር ያለ መሆኑ ተገልጿል።

 የከተማዋን ከንቲባ የአብዲ ዒሌ ታጣቂዎች ለመግደል ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ተከትሎም ተቃውሞ መባባሱን የኢሳት ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም የአብዲ ዒሌ ሚሊሺያ ሀይል በህዝቡ በደረሰበት ተቃውሞ ከተማዋን ለቆ መጣቱ ታውቋል። አይሻ ላይ ባለው ውጥረት የተነሳም ኢትዮጵያን ከጅቡቲ የሚኣገናኘው ዋናው መስመር ተዝግቶ ውሏል።

በሽንሌ፣ በፍዴር፣ በሊበን፣ በሸበሌና በኤረር ዞኖች የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ዒሌ ከስልጣን እንዲወርዱ በምጠየቅ ህዝቡ ዳግም የጀመረው ተቃውሞ ተቀጣጥሏል።

 ከትላንት ምሽት ጀምሮም አቶ አብዲ ዒሌ የልዩ ሃይልና የሚሊሺያ ሰራዊታቸውን የተቃውሞ ማዕከል ወደ ሆነችው የሽንሌ ዞን በማሰማራ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል።

በአብዲ ዒሌ የተላኩት የልዩ ሃይልና የሚሊሺያ ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ጥቃት የተነሳ ከ10ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪ ወደ ጅቡቲ መሰደዱም ታውቋል።

ቁጡ እየጨመረ በመሆኑ ትክክለኛውን አሀዝ ማግኘት እንዳልተቻለ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ጥቃቱን በመሸሽ የተሰደዱት የክልሉ ተወላጆች በጅቡቲ የድንበር ከተማ አሊሰቢህ ተጠልለው እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በተለይም በደወሌ፣ አይሻና በአብዛኛው ከሽንሌ ዞን የሚሰደዱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ከሌሎች የክልሉ አከባቢዎችም ጥቃት በመሸሽ ወደ ድንበር የሚሰደዱ ሰዎች እንዳሉ ተገልጿል።

በአብዲ ዒሌ ሃይሎች የተከፈተውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም የፌደራል ፖሊስ ጥረት ችእያደረገ እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና በአከባቢው የተሰማራው የፌደራል ፖሊስ ሃይል አነስተኛ በመሆኑ ጥቃቱን ለማስቆም እንዳልቻለ ተመልክቷል።

በተያያዘ ዜና በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ያለውን የሰላም ኮንፈረንስ ለማወክ የአብዲ ዒሌ ልዩ ሃይል ሰራዊት የወሰደው እርምጃ መክሸፉ ተገልጿል። በሶማሌ ክልል አክቲቪስቶች የተዘጋጀውና ከ1500 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበትን የሰላም ኮንፈረንስ ለማስቆም ጠረት ያደረገው የክልሉ ልዩ ሃይል በፌደራል ፖሊስ በተወሰደ እርምጃ እንዳልተሳካ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ስብሰባው ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ በሶማሌ ክልል የሰፈነውን ቀውስ ለመፍታት እየመከረ ይገኛል።

No comments:

Post a Comment