(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 25/2010) በኢትዮጵያ ያለ ስራ ሃላፊነታቸው በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ሚኒስትሮች ፍትህን ሲያዛቡ መቆየታቸውን የቀድሞው የሃገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ ገለጹ።
ከነዚሁ ሚኒስትሮች መካከልም ያለሃላፊነታቸው የታክስ አቤቱታ የሚሰሙ፣ጨረታ ተከለከልኩ ያሉትን አቤቱታ በመቀበል በአማላጅነት ጣልቅ የሚገቡት አቶ በረከት ስምኦን ነበሩ ብለዋል።
አቶ መላኩ ፈንታ የአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት ወይዘሮ አሰፉ ፈንቴ ዘመናዊ የፊልም ካሜራ ያለቀረጥ ሊያስገቡ ሲሉ በመያዛቸውና እንዲወረስ በማድረጋቸው በአቶ በረከት ጥርስ እንደተነከሰባቸውም ገልጸዋል።
የቀድሞው የኢሕአዴግ አመራር አቶ በረከት ስምኦን የማስታወቂያና የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር በመሆን ሰርተዋል።
በኋላ ላይም በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ውስጥ በምክትል ዳይሬክተርነት ሲሰሩ ቆይተዋል።
አቶ በረከት ውስን የስራ ሃላፊነት ቢኖራቸውም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው ቀረቤታ ምክንያት አንጋሽና አውራጅ ሆነው በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባትም ይታወቃሉ።
የቀድሞው የኢሕአዴግ ስራአስፈጻሚ አባል የነበሩትና የብአዴን ከፍተኛ አመራር ሆነው ያገለገሉት አቶ መላኩ ፈንታ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ይህንኑ የሚያረጋግጥ መግለጫ ለአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል።
የሃገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መላኩ ፈንታ አቶ መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ትናንሽ መንግስታት ተፈጥረዋል።
በማይመለከታቸው ጉዳይ የሚገቡ ሚኒስትሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በማይመለከታቸው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የታወቁት ደግሞ አቶ በረከት ስምኦን መሆናቸውን አቶ መላኩ ፈንታ ተናግረዋል።
የእስር አያያዛቸውን በተመለከተ አቶ መላኩ ፈንታ ተጠይቀው በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሳይወሰን በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚነታቸውም ሳይጠየቁ ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነካ በወረራና በከፍተኛ አጀብ መታሰራቸውን አስታውሰዋል።
ይህ ለምን ሆነ ተብሎ ሲጠየቁ አሁን እኔ በሌለሁበት ያለአግባብ ታገድኩ ያሉት አቶ በረከት የኔ መታሰር አግባብ መሆኑን ሲከራከሩና መልስ ሲሰጡ የነበሩ እሳቸው ናቸው ብለዋል።
No comments:
Post a Comment