( ኢሳት ዜና ነሐሴ 23 ቀን 2010 ዓ/ም ) የቀድሞው የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትና በተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚወነጀሉት አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ የወንጀል ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጥያቄ አቅርበዋል። አቶ አብዲን ጨምሮ ወይዘሮ ራሃማ መሐመድ፣ አቶ አብድራዛቅ ሰህኒ እና አቶ ሱልጣን መሐመድ ችሎት የቀረቡ ሲሆን፣ ባለስልጣኖቹ ከጤና ጋር በተያያዘ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ለመመልከት ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል። ፖሊስ ግለሰቦቹን ለፍርድ ያቀረበው ዜጎችን እየለዩ በማፈናቀል፣ ዘርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃቶች እንዲፈጸሙ፣ አብያተክርስቲያናት እንዲቃጠሉ በማድረጋቸው መሆኑን ጠቅሷል። አቶ አብዲ ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ በክልሉ ውስጥ ሲፈጸሙ ለቆዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዋነኛው ተጠያቂ ተደርገው ይቆጠራሉ። ሂውማን ራይትስ ወች ባወጣቸው የተለያዩ የምርመራ ሪፖርቶች የክልሉ ባለስልጣናት ተጠያቂ እንዲሆኑ ሲያሳስብ ቆይቷል።
No comments:
Post a Comment