Thursday, August 9, 2018

የቀብሪዳሃር ስደተኞች ለከፍተኛ ችግር መጋለጠቸውን ገለጹ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 3/2010) በቀብሪዳህር መከላከያ ሰራዊት ግቢ የተጠለሉ ዜጎች የሰራዊቱ ቀለብ እየተመናመነ በመምጣቱ ለከፍተኛ ችግር መጋለጠቸውን ገለጹ።

ላለፉት ስድስት ቀናት ሰራዊቱ ቀለቡን እያካፈላቸው መቆየቱን ተፈናቅዮች ገልጸዋል። ከ5ሺህ በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ቤት ንብረታቸው ተዘርፏል።


ህይወታቸውን ለማትረፍ በአቅራቢያው በሚገኝ መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ተሸሽገው ይገኛሉ።

በሌላ በኩል በጂጂጋ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ ሁኔታ ቢኖርም የምግብና የውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ችግሩ እየከፋ መምጣቱን ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ቀብሪዳህር ከጂጂጋ በ382 ኪሎ ሜትር ይርቃል።

የሰሞኑ ጥቃት ብርቱ ስጋት ከደቀነባቸው አከባቢዎች ቀብሪዳህር አንዱ በመሆን ይጠቀሳል።

ባለፈው ቅዳሜ ቤት ንብረታቸው ሲዘረፍባቸውና ጥቃት ሲሰነዘርባቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ በ2ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ የተሸሸጉት ከ5ሺህ በላይ ዜጎች የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው።

በትላንትናው ዕለት ኢሳት በካምፕ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ዜጎችን ባነጋገረ ጊዜ የመከላከያ ሰራዊቱን ቀለብ እየተሻሙ ያለፉትን አራት ቀናት መግፋታቸውን ግልጸው እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ተፈናቃይ ዜጎች በዛሬው ዕለት እንደገለጹት እየተሻሙት ያለው የመከላከያ ሰራዊት ቀለብ እየተመናመነ መጥቷል።

ሰራዊቱ ከራሱ በላይ ለተፈናቀሉት በማሰብ ቀለቡን ያካፈላቸው በመሆኑ የተመደበው ኮታ በማለቅ ላይ መሆኑን የጠቀሱት ተፈናቃይ ዜጎች በቀጣይ የረሃብ አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን በስጋት ይገልጻሉ።

በቀን አንድ ጊዜ በመብላት ህይወታቸውን ማቆየት የቻሉ ቢሆንም አስቸኳይ እርዳታ ካልተደረገላቸው ሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል ይላሉ።

እስከአሁን ከፌደራል መንግስት የደረሰላቸው ምንም ድጋፍ እንደሌለም ጠቅሰዋል።

ከቀብሪዳህር በተጨማሪ በዋርዴርና በሌሎች አከባቢዎችም የክልሉ ተወላጅ ባልሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ አደጋ መደቀኑን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ከዋና ከተማዋ ጂጂጋ ራቅ ባሉ አከባቢዎች የመረጃ ክፍተት በመኖሩ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማወቅ እንዳልተቻለም ይነገራል።

መንግስት አስቸኳይ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጥም በቀብሪዳህር የተሸሸጉ ዜጎች ጥሪ አድርገዋል።

በተያያዘ ዜና በጂጂጋ ምግብና ውሃ የማቅረቡ ተግባር ዛሬ መጀመሩ ታውቋል።

በተለይም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ወደ ጂጂጋ መግባቱ በተፈናቀሉ ዜጎች ላይ ይደርስ የነበረው የሰብዓዊ ቀውስ ለጊዜው መቅረቱን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት በሶማሌ ክልል የተከሰተውን አደጋ የተመለከተ ኮሚቴ ማቋቋሙም ተገልጿል።

ኮሚቴው በሁለት ምዕራፎች ድጋፍ ለማድረግ የተቋቋመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን አስቸኳይ የምግብና አልባሳት ድጋፍ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚሰራበት ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

በሁለተኛው ምዕራፍም የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ከጂጂጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ሀረር ከተማ መግባታቸውን የደረሰን ዜና አመልክቷል።

በሀረር ትምህርት ቤቶች የተጠለሉት የጂጂጋ ተፈናቃዮችን የሀረር ከተማ ህዝብ ጊዜያዊ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment