Tuesday, August 14, 2018

በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከጅቡቲ እየወጡ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 8/2010) በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየዕለቱ ከጅቡቲ በመውጣት ወደ ሀገር ቤት እየገቡ መሆናቸው ተገለጸ።
ፋይል በምስራቅ ኢትዮጵያ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ የሚደርሰውን ጥቃት በመፍራት በርካታ ኢትዮጵያውያን ጅቡቲን ለቀው መውጣታቸውን ቀጥለዋል።
በድሬዳዋ አምስት የጅቡቲ ዜጎች ባለፈው ሳምንት መገደላቸውን ተከትሎ በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥቃት እየተፈጸምብን ነው ሲሉ ለኢሳት ገልጸዋል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከጅቡቲ ተፈናቅለው በምስራቅ ኢትዮጵያ በተለያዩ አከባቢዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል።
በጅቡቲ ከ800ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
አብዛኞቹ በህገወጥ መንገድ የገቡ በመሆኑ ቁጥሩ ከተጠቀሰው በላይ ሊልቅ እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲፈጠር እንደአንድ መሸሸጊያ ሆና ኢትዮጵያውያንን ስታስጠልል ቆይታለች- ጅቡቲ።
ከቀድሞው የህወሀት መንግስት ጋር በነበራት ግንኙነት ጅቡቲ ለኢስትዮጵያውያን የዲሞክራሲና የነጻነት ታጋዮች የምትመች ሀገር አልሆነችም።
ህይወታቸውን ለማትረፍ የተጠጓትን ኢትዮጵያውያን አሳልፋ ስትሰጥ እንደነበር ይታወቃል። ሰሞኑን ደጎም የምስራቅ ኢትዮጵያው አለመረጋጋት በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለከፍተኛ ጥቃት ማጋለጡ እየተነገረ ነው።

የጥቃቱ አንዱ መንስዔ በሶማሌ ክልል ከተፈጠረው ግጭት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ቢነገርም በአፍርካው ቀንድ አዲስ በመጣው የለውጥ አካሄድ የጅቡቲ መንግስት ደስተኛ አለመሆኑ ያስከተለው የበቀል እርምጃም ሊሆን እንደሚችል ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች ይገልጻሉ።
በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ምስራቅ አፍሪካን ወደ አዲስ የሰላምና የትብብር ቀጠና ለመቀየር የጀመሯቸው እንቅስቃሴዎች በጅቡቲ መንግስት ዘንድ ምቾት የሚሰጥ እንዳለሆነ መረጃዎች ያመልክታሉ።
ሁለቱ ምክንያቶች ተጠቅሰው ከሰሞኑ የኢትዮጵያውያኑ መፈናቀል ጋር እየተነሳ ነው። የአብዲ ዒሌ ደጋፊ ናቸው የሚባሉና በጅቡቲም የጎሳ ሀረግ ያላቸው ጅቡቲያውያን በተለይም በኦሮሞ ተወላጅ በሆኑ ኢትዮያውያን ላይ ጥቃት መክፈታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንም ለማወቅ ተችሏል። በየዕለቱ ከ500 እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየተሰደዱ ነው ተብሏል።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ጅቡቲን ለቀው መውጣታቸው ታውቋል።
ስሙ እንዲገለጽ ያለፈለገ በጅቡቲ ነዋሪ የሆነ አንድ ኢትዮጵያዊ ለኢሳት እንደገለጸው ይፋ ያልሆነ የበቀል እርምጃ በጅቡቲ በኩል እየተወሰደ ነው።
ባለፈው ሳምንት በድሬዳዋ 5 የጅቡቲ ዜጎች መገደላቸው በኢትዮጵያውያን ላይ ጥቃቱ እንዲባባስ እንዳደረገውም ይነገራል።
በተያያዘም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲስ አቅጣጫ እየተነሳ በጅቡቲ ታጣቂዎች በኩል ኢትዮጵያውያንን ዒላማ ያደረገ እርምጃ መወሰዱ ችግሩን እንዳባባሰው ኢሳት ያነጋገረው ነዋሪ ገልጿል።
በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተፈጠረው ችግር አንጻር የወሰደው እርምጃም እንደሌለ ታውቋል።
ኢሳት በትላንትናው ዘገባው ከጅቡቲ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሀረርጌ አሰቦት በየትምህርት ቤቱ ተጠልለው እንደሚገኙ መግለጹ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment