Thursday, August 2, 2018

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልዩነታቸውን አስወግደው በጋራ ለመስራት ተስማሙ

Image may contain: 11 people, people smiling, indoor(ኢሳት ዲሲ--ሐምሌ 26/2010) በሰሜን አሜሪካ የሚንቀሳቀሱ አራት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ልዩነታቸውን አስወግደው በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
ሂጅራ ፋውንዴሽን፣ በድር ኢትዮጵያ፡ ሰላም ፋውንዴሽንና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊ ህብረት በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባትና ልዩነት በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ከተነጋገሩ በኋላ አንድነታቸውን የሚያረጋግጡ ስምምነቶች ላይ ደርሰዋል።
አራቱን የኢትዮጵያ ሙስሊም ተቋማትን በመሽምገል ከስምምነት እንዲደርሱ ያደረጉት ከሀገር ቤት የመጡት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መሆናቸውም ታውቋል።
ትላንት እዚህ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ አራቱን የኢትዮጵያ ሙስሊም ድርጅቶችን ወደ ስምምነት እንዲመጡ የሸመገሉት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።
ሰብሳቢው ኡስታዝ አቡበክር አህመድ፣ ኡስታዝ ኢንጅነር በድሩ ሁሴንና ኡስታዝ ነቢዩ አያሌው የስምምነት ውይይቱን በመምራት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፣ ባድር ኢትዮጵያ፣ ሰላም ፋውንዴሽንና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊ ህብረት ለዓመታት በተናጠል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የጋራ መግለጫው አመልክቷል።
በሀገር ቤት ሙስሊሙን ማህበረሰብ በሚመለከቱና አጠቃላይ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የየድርሻቸውን ሲወጡ እንደነበርም አስታውሷል።
በእነዚህ ዓመታት የአካሄድ ልዩነቶችና ቅራኔዎች ተፈጥረው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንዳይችሉ እንዳደረጋቸውም ተጠቅሷል።
ይህን ችግር ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመፍታት በፈርስት ሂጅራ 30ኛው ዓመት ክብረ በዓል ጀምሮ በ18ኛው የበድር ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ጎን ለጎን በቀላሉ ሊቀረፉ ያልቻሉ የውስጥ ችግሮችንን ዋና ምክንያት በመለየት ዳግም እንዳይከሰቱም መፍትሄ ማግኘትን ታሳቢ ያደረገ ጥረት መደረጉን በጋራ መግለጫው ላይ ተመልክቷል።
ይህ ጥረት በተለይም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ኡስታዝ ነቢዩ አያሌው እና ኡስታዝ በድሩ ሁሴን አወያይነት በድር ኢትዮጵያ፣ ፈርስት ሂጅራ ፋውንዴሽን፣ ሠላም ፋውንዴሽን እና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ ደጋፊ ህብረትን ያካተተ የአራትዮሽ ውይይት እና ሽምግልና ተካሂዶ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው መግለጫ ያመለከተው።
ያለፉ ቁርሾዎችና ክስተቶች ከዚህ በኋላ አጀንዳ ተደርገው እንዳይነሱ ድርጅቶቹ ተስማምተዋል።
በመካከላቸው ቅራኔ የሚፈጥሩ ከየትኛውም ወገን የሚቀርቡ አፍራሽ ሀሳቦች በቅድሚያ በቀጥታ የሚመለከተው አካል በተጨማሪም ድርጅቶቹ በጋራ ሆነው የማስተካከል ኃላፊነት እንዲወስዱ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በድርጅቶቹ መካከል የተሻለ መተማመን ለመፍጠርም አሉታዊ ሀሳቦችና ተግባራት ሲታዩ ድርጅቶቹ አባላቶቻቸውን በመምከር በመካከላቸው ያለውን ትስስር በመተማመን ላይ ተመስርቶ እንዲጠናከር በሚያስችል መስመር እንዲጓዙ ሁሉም ወገን ስምምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
ስምምነቱን ዘላቂ ለማድረግ እንዲሁም የድርጅቶቹን አቅም ለማሳደግ በባለሙያዎች በሚዘጋጅ ጥናት ላይ በመመርኮዝ ድርጅቶቹን በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችሉ መዋቅራዊ ለውጦች እንዲደረጉም ከስምምነት ላይ መደረሱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment