(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 25/2010) ከግንቦት 7 አመራሮች ጋር ውጤታማ የሆነ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
አመራሮቹም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሃገራቸው ጉዳይ ላይ በንቃት እንደሚሳተፉም አመልክተዋል።
አክቲቪስት ታማኝ በየነ እንዲሁም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጅዋር መሃመድ ወደ ሃገራቸው እንደሚመለሱም ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።
ለሳምንት ያህል በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲወያዩ የቆዩትና ዛሬ አዲስ አበባ የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰጡት መግለጫ ቆይታቸው የተሳካና ውጤታማ እንደነበርም አመልክተዋል።
በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መኩራታቸውንና ይበልጥ ሃላፊነት እንዲሰማቸው እንዳደረግዋቸውም ገልጸዋል።
በአሜሪካ ቆይታቸው ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
አመራሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጁ እንደሆኑ እንዳረጋገጡላቸውም ጠቁመዋል።
የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ትላንት በሰጡት መግለጫ በአንድ ወር ግዜ ውስጥ ወደ ሃገር ቤት እንደሚመለሱ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች በተጨማሪ አክቲቪስት ታማኝ በየነና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅና አክቲቪስት ጅዋር መሐመድም በተመሳሳይ በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት እንደሚገቡም ገልጸዋል።
በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ለአዲሱ አመት እንደሚገቡ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሃገር ቤት የሚገኙ ባለሆቴሎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የዋጋ ቅናሽ ጭምር በማድረግ ወገናዊነት እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment