(ኢሳት ሐምሌ 26/2010)በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ 1948 ዓ.ም የተወለደው አንጋፋው የመድረክ ፈርጥ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም ባጋጠመው የኩላሊት ህመም በተወለደ በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ላለፍት 42 ዓመታት የመድረክ ንጉስ እንደነበር በሙያ ባልደረቦቹና በጥበብ አድናቂዎች የተመሰከረለት ፍቃዱ ተክለማሪያም ኦቴሎ፣ ኤዲፐስ ንጉሥ፣ ሐምሌት፣ ቴዎድሮስ፣ ንጉሥ አርማህ፣ መቃብር ቆፋሪውና የሬሣ ሳጥን ሻጩ፣ የሠርጉ ዋዜማ፣ ባለ ካባና ባለ ዳባ፣ መልዕክተ ወዛደር የመሳሰሉት ወጥና ትርጉም ተውኔቶች ከተሳተፈባቸው ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። ከተውኔናትና ቴያትር በተጨማሪም በሬድዮ የመጽሐፍት ዓለም ትረካ፣ በቲቪና በሬድዮ ተከታታይ ድራማዎችን ጨምሮ፤ በወጥ የአማርኛ ፊልሞች ላይ ተዋናይ በመሆንም አገልግሏል። ፍቃዱ ህክምናውን ባህር ማዶ ሄዶ እንዲታከም ለማስቻል በተዘጋጀው የገቢ በማሰባሰብ ስነስርዓት ላይ ያገኘውን 200 ሽህ ብር ገንዘብ ለኩላሊት ታማሚ ታዳጊ ልጅ በመስጠት ቅንነቱንና ለጋስነቱንም አስመስክሯል። አንጋፋው የጥበብ ሰው ፍቃዱ ተክለማሪያም ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ወዳጅ ዘመዶቹና የሙያ አድናቂዎቹ በተገኙበት የቀብር ስነስርዓቱ ተፈፅሟል። የዝግጅት ክፍላችን ለመላው ቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
ባለ ካባ ና ባለ ዳባ
ReplyDelete