Monday, August 13, 2018

ከጅቡቲ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተፈናቀሉ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 7/2010) ከጅቡቲ ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጸ።

በአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ጥቃትን ሸሽተው የተሰደዱ መሆናቸው ታውቋል።

በምዕራብ ሀረርጌ አሰቦት በትምህርት ቤቶች ተጠልለው የሚገኙት የጅቡቲ ተፈናቃዮች ምግብና ውሃ አጥተው በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።


በሌላ በኩል በምስራቅ ሀረርጌ ትላንት በተፈጸመ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል። ጥቃቱን የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል መፈጸሙን መረጃው አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ውጥረት ድንበር ተሻግሮ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው። በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል የተነሳው ግጭት ጅቡቲ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ማምጣቱን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው ።

 በሰሞኑ ግጭት በቀል እየተፈጸመብን ነው ባሉ የአንድ ብሄር አባላት ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጹ ኢትዮጵያውያን የኦሮሞ ተወላጆች ከሚኖሩበት ጅቡቲ ሸሽተው ወደ ሀገር ቤት በመሰደድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ባለፉት አምስት ቀናት ከ30ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከጅቡቲ መሸሻቸውንና በአሰቦት አከባቢ ተጠልለው እንደሚገኙ ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ገልጸዋል።

እነዚህን ዜጎች በአሰቦት ከተማና በዙሪያዋ ባሉ ትምህርትቤቶች ውስጥ በማስጠለል ጊዜያዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

በአሰቦት ከተማ የውሃ አቅርቦት ከተቋረጠ ከ15 ቀናት በላይ በመሆኑ ከጅቡቲ ተፈናቅለው ለመጡት ዜጎች የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት እንዳልተቻለ ጉዳዩን የሚከታተሉት የአሰቦት ከተማ ነዋሪ ለኢሳት ገልጸዋል።

የምግብና የውሃ ችግር ተፈናቃዩቹን አደጋ ላይ በመጣሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቧል። ከጅቡቲ ሸሽተው ኢትዮጵያ የገቡት ዜጎች እንደሚሉት በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለው መንገድ ላይ ቀርተዋል።

አሁንም ጥቃቱ ባለመቆሙ ዜጎች ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ናቸው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። በሚቀጥሉት ቀናት ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር የሚጨምር በመሆኑ የሰብዓዊ ቀውስ ሳይከሰት መንግስት መፍትሄ እንዲሰጥ ተጠይቋል።

በሌላ በኩል በምስራቅ ሀረርጌ ዞን መዩ ሙለቂ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ቢቢሲ ኦሮምኛ እንደዘገበው በታጠቁ ሃይሎች በተፈጸመው ጥቃት ህጻናትና አዛውንቶችን ጨምሮ ከ30 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

 በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። ጥቃቱን የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ፈጽሞታል የሚል መረጃ እንዳለም ተጠቅሷል።/ምስሉ ከቆየ መረጃ ላይ የተወሰደ ነው/

No comments:

Post a Comment