Tuesday, August 14, 2018

በቴፒ ከተማ የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ 4 ሰዎች ተገደሉ

Image may contain: 1 person, sitting and selfie(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 8/2010) በደቡብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን በቴፒ ከተማ የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ 2 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
ብሄር ተኮር ባሆነው በዚሁ ጥቃት የቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ስጋት ውስጥ መሆናቸው ታውቋል። ነዋሪው ራሱን ለመከላከል እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
መኖሪያና ንግድ ቤቶች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከፍተኛ ውድመት መድረሱን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የደኢህዴን ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በከተማዋ ተገኝተው ሁኔታውን ለማረጋጋት ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱም ታውቋል።
በዘር አትከፋፍሉን በሚል የከተማው ነዋሪ ተቃውሞን እያሰማም ነው ተብሏል።
በሸካ ዞን ዘርን ያተኮረ ጥቃት ሲከሰት የሰሞኑ የመጀመሪያው አይደለም። በየዓመቱ ወቅት እየጠበቀ የሚከሰት ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ምክንይስት ሰበብ የሆነ ችግር ነው።
የዘንድሮው ግን የከፋ ነው ይላሉ ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ያዝ ለቀቅ ሲያደርገው የሰነበተው ጥቃት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ወደለየለት ብሄር ተኮር ጥቃት ተለውጦ በቴፒና በዙሪያዋ የሚገኙ መንደሮች ላይ ከፍተኛ አደጋ ማንዣበቡን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ከትላንት በስቲያ በቤት ግንባታ ስራ በተሰማሩ ወጣቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም የተጀመረው አለመረጋጋት ወደለየለት ቀውስ እንዳይሸጋገር ስጋታቸውን የሚገልጹ ነዋሪዎች የፌደራል መንግስት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።
በዛሬው ዕለት በተፈጸመ ጥቃት 2 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ዘግይተው በወጡ ዜናዎች የተገደሉት ሰዎች ቁጥር አራት መድረሱ ታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደሚገልጹት በዘር ላይ ያተኮረው አስተዳደር ህዝቡ እንዲገፋ አድርጎታል።
በሸካ ዞን ውስጥ ተወልዶ ያደገ የሌላ ብሄር ተወላጅ የትምህርትም ሆነ የስራ እድል እንዲነፈግ ይደረጋል።
ወጣቱ በተወለደበትና ባደገበት አከባቢ ስራ ባለማግኘቱ ወደሌሎች የሀገሪ ክፍሎች መሰደድ እጣ ፈንታው ሆኗል ይላሉ።
መብታችንን ብንጠይቅ የሚደርስብን ቅጣት እስከሞት የሚደርስ ነው የሚሉት ነዋሪዎች አከባቢውን ለቀን እንድንወጣ የሚደረገው ጫና በዞኑ አመራሮች አማካኝነት የሚፈጸም ነው ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት ወደ ቴፒ የመጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የከተማዋን ነዋሪዎች ቢያነጋግሩም መፍትሄ ሊሰጡት አልቻሉም ይላሉ ኢሳት ያነጋገራቸው።
የእሳቸውን መመለስ ተከትሎ በአከባቢው መጠነ ሰፊ ጥቃት መከፈቱን የሚገልጹት ነዋሪዎች ዛሬ ከተገደሉት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ሰዎችም በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ማለፉን ጠቅሰዋል።
በጥቃቱ የልዩ ሃይልና የፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎችም መሳተፋቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ጥቃቱን ተከትሎ በቤተክርስቲያን ተጠልለው የሚገኙት የአከባቢው ነዋሪዎች መንግስት በፋጣኝ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎች በቴፒ ከተማ በዘረፋ ተግባር ተሰማርተው ሱቆችንናና መደብሮችን ሰብረው እቃ በመጫን እየወሰዱ መሆኑም ተገልጿል።

No comments:

Post a Comment