Thursday, August 2, 2018

በቤንሻንጉል 108 ሲቪሎች እና ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 26/2010) በቤንሻንጉል ክልል ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ 108 ሲቪሎች እና ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ ።
የቤንሻንጉል ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አሻድሊ ሃሰን ዛሬ አዋሳ ላይ እንደተናገሩት ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 20 ፖሊሶች እና 88 ሲቪሎች ታስረዋል።
ግጭቱን የፈጠሩት ለውጡን ያልተቀበሉ እና ሥልጣን የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል።
ባለፈው ሰኔ የቤንሻንጉል ክልል ዋና ከተማ በሆነችው አሶሳ በተከሰተው ግጭት 14 ያህል ሰዎች ሲገደሉ ፣ወደ 70 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ለግጭቱ መቀስቀስና መባባስ ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና የጸጥታ ባለስልጣናት ወዲያወኑ መታሰራቸውም ይታወሳል።
የቤንሻንጉል ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አሻድሊ ሃሰን በወቅቱ በሰጡት መግለጫ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ከሥራ እና ሥልጣናቸው ሲታገዱ ፣የክልሉ ልዩ ሃይል ፖሊስ ሃላፊዎችም ከስልጣናቸው መነሳታቸውን አስታውቀው ነበር።

በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ 54 የክልሉ ባለሥልጣናት ሲታሰሩ፣አስራ አንድ ፖሊሶችም በተመሳሳይ መታሰራቸውን በወቅቱ አስታውቀዋል።
አሶሳ እየተካሄደ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ እንደተገለጸው የታሳሪዎቹ ቁጥር 108 ደርሷል።
ባለስልጣናትን ጨምሮ 88 ሲቪሎች ሲታሰሩ ፣ሃላፊዎችን ጨምሮ የታሰሩ የፖሊስ አባላት 20 መሆናቸው ተመልክቷል።
የሃዋሳውን ግጭት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ ግጭቱን የሚያቀነባብሩትን ሃይሎች የቀን ጅቦች ሲሉ መጥቀሳቸው ይታወሳል።
በየክልሉ በተለይም በዳር ሃገር ጸጉረ ልውጦችን ሕብረተሰቡ እንዲከታተል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment