(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 25/2010) በኢትዮጵያ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት እንደጠላት ማየት አለብን ሲሉ የቀድሞ የኢንሳ ዳይሬክተር ጄነራል ገለጹ።
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከስልጣናቸው የተነሱት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት መረብ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ድምጸ ወያኔ ለተሰኘው የህወሀት ልሳን ሬዲዮ ጣቢያ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ እንደገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የኢህአዴግ ሽታ እንኳን የሌለው ነው።
ህገመንግስታዊ ስርዓቱን እየበላ ያለ መንግስትም ነው ብለዋል የቀድሞ የኢንሳ ዳይሬክተር።
ይህን እንደጠላት ሃይል አድርገን ካልወሰድነው እንዴት አምርረን እንደምንዋጋው ግልፅ ሊሆንልን አይችልም በማለትም ገልጸዋል።
የቀድሞ የኢንሳ ዳይሬክተር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ለድምጸ ወያኔ በሰጡት ቃለመጠይቅ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አስተዳደር በጊዜ ካላስተካከልነው መጨረሻው አደገኛ ሃይል ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አሁን የሚታዩት ሁኔታዎች አስቀያሚ ናቸው በማለት የገለጹት ሜጀር ጄነራል ተክለብርሃን፡ እንደእሬት ከሚመር እውነት ጋር ተፋጠናል ብለዋል።
ኢህአዴግ በስብሶ የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱንም የቀድሞ የኢንሳ ዳይሬክተር ገልጸዋል። ኢህአዴግ አሁን የተያያዘው አካሄድ በትግራይ ህዝብ ደም የመጣን ህገመንግስታዊ ስርዓት እየበላው ነው፡ የበላይነት ያገኘው ሃይል ከህወሀት ጋር አንድ ያልሆነ ሃይል ነው ብለዋል በቃለመጠይቁ።
አሁን ያለውን ስርዓት ማየት ያለብን እንደጠላት ሃይል ነው ያሉት ሜጄር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ይህን ሃይል እንደጠላት አድርገን ካልወሰድነው እንዴት አምርረን እንደምንዋጋው ግልጽ ሊሆንልን አይችልም በማለት ገልጸዋል።
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው ሃይል የኢህአዴግን ፕሮግራምን እየበላ የጨረሰ፡ የኢህአዴግ ሽታ እንኳን የሌለው ቡድን ነው ብለዋል።
ለእኔ ይህ የጠላት ሃይል ነው – እንደጠላት ልንወስደው ይገባል ሲሉ ለድምጸወያኔ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ ገልጸዋል።
ኢህአዴግ ካልሆነ ህዝባዊ አይሆንም ያሉት ሜጀር ጄነራል ተክለብርሃን ይህ ሃይል ሄዶ መጨረሻው ፌደራል ስርዓቱን ሊያጠፋው እንደሚችል መታወቅ አለበት ብለዋል።
አሁን ያለው ስርዓት የግለሰብ ፍጹም ገዥነትና አንበርካኪነት የተንጸባረቀበት ነው በማለትም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን መንግስት ተችተዋል።
የመንግስታችንን ስርዓት ትርጉም ወደ ሌለው ደረጃ አውርዶታል፡ አሁን ኢህአዴግ የሚባል ጠፍቷል ብለዋል የቀድሞ የኢንሳው ዳይሬክተር ተክለብረሃን ወልደአረጋይ። የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች ምልክት ብቻ ሆነው ቀርተዋል፡፡
በአጭሩ የንጉሰነገስት አገዛዝ ተመስርቷል ነው ያሉት ጄነራሉ። የኢትዮጵያንንና የኤርትራን ጉዳይ ህዝብ ሳይመክርበት ብቻውን ወስኗል ብለውም ዶ/ር አብይ ላይ ጣታቸውን ጠንቁለዋል። የሰኔ 16ቱንም የአዲስ አበባ የድጋፍ ሰልፍ በጽኑ ኮንነውታል።
የህግ የበላይነት ጠፍቷል። መንግስትን በሃይል ለመገልበጥ የሞከሩ ወንጀለኞች ተፈተዋል በማለት በቁጭት የተናገሩት ሜጄር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ይህ አካሄድ በጣም አደገኛ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በሰኔ 16 የተፈጸመውን የቦንብ ጥቃት ለመመርመር አዲስ አበባ የገቡትን የኤፍ ቢ አይ መርማሪዎችንም በተመለከተ በጽኑ አውግዘዋል።
ከኤፍ ቢ አይ የተሻለ ተቋም ገንብተን በራሳችን ምርመራውን ማድረግ ሲገባን ለውጭ አሳልፈን የምንሰጥ ከሆነ ጥገኝነት ነው ብለዋል የቀድሞ የኢንሳ ዳይሬክተር ጄነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ።
የመጀመሪያ ክፍል ቃለመጠይቁ በህወሀት ልሳን በሆነው ድምጸ ወያኔ የተላለፈ ሁለተኛውና ቀጣይ ክፍል ከሰሞኑ ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment