(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 28/2010) ሰሞኑን በድንበር ላይ በሱዳን ታጣቂዎች የተገደሉ ኢትዮጵያውያን የቀብር ስነስርዓታቸው ተፈጸመ።
በመተማ ወረዳ ገንዳውሃ ከተማ በተፈጸመው የቀብር ስነስርዓት በብዙ ሺህ የሚቆጠር የአካባቢው ነዋሪ በተኩስ እሩምታ በማጀብ ማከናወኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በተለይም የአርበኛ ገብሬ አውለው የቀብር ስነስርዓት በልዩ ስሜት የተከናወነ ሲሆን ህዝቡ ድንበር ጥሶ ጥቃት የፈጸመውን የሱዳን ጦር ለመፋለም መዘጋጀቱን አስታውቋል።
በቀብር ስነስርዓቱ ላይ በቀረርቶና ሽለላ ጀግኖቻቸውን የሸኙት የመተማ ወረዳ ነዋሪዎች የሱዳን ታጣቂዎች በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አለበለዚያ ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል ዳርድንበራቸውን እንደሚያስከብሩ ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና በወሎ ሃይቅ ከተማ የህዝብ ቁጣ ተቀስቅሷል። የከተማው የመንግስት አመራሮች ከስልጣን እንዲወርዱ በሚይጠቀው ህዝባዊ ቁጣ የሀይቅ ከተማ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶባት መዋሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የመሬት ወረራው ይቁም፣ የህወሃት ሰዎች አይመሩንም፣ በረከት ስምዖን አይመራንም፣ የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።
ከደሴ ወልድያ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል። የአማራ ልዩ ሃይል መለዮ የለበሱ ታጣቂዎች በህዝቡ በተለይ በወጣቱ ላይ ቤት ለቤት እየዞሩ ድብደባ መፈጸማቸው የተገለጸ ሲሆን የአስለቃሽ ጭስ በህዝቡ ላይ መወርወሩንም ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያስረዳል።
No comments:
Post a Comment