Monday, July 2, 2018

የአዲስ አበባውን የድጋፍ ሰልፍ ያስተላለፉ መገናኛ ብዙሃን ሊጠየቁ ይገባል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 25/2010) የአዲስ አበባውን የድጋፍ ሰልፍ ያስተላለፉ መገናኛ ብዙሃን ሊጠየቁ ይገባል ሲል የትግራይ ክልል ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ገለጸ።
ድርጅቱ ከብሮድካስት ባለስልጣን የዕለቱን ትዕይንት ሽፋን ያልሰጠበትን ምክንያት እንዲያብራራ በደብዳቤ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ ላይ እንደገለጸው በህግ የተከለከለ ሰንደቅ ዓላማን ጨምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ የተባሉ ድርጅቶች አርማዎች የሚታይበትን ሰልፍ ያስተላለፉ የመገናኛ ብዙሃን መጠየቅ እንደሚገባቸው ጠቅሷል።
የትግራይ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የትላንቱን የባህርዳርን የድጋፍ ሰልፍ እንዳላስተላለፈም ታውቋል።
ሰኔ 16 በአዲስ አበባ የተካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ በተመለከተ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን በልዩ ትኩረት ክስተቱን በቀጥታ ሽፋን ማስተላለፋቸውን በመጥቀስ የትግራይ ቴሌቪዥንና ኢ ኤን ኤን የተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለሰልፉ ሽፋን የነፈጉበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ብሮድካስት ባለስልጣን መጠየቁ የሚታወስ ነው።

ኢ ኤን ኤን የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ለብሮድካስት ባለስልጣን ጥያቄ ይፋዊ ምላሽ ሳይሰጥ ባለፈው ሳምንት ሰራተኞቹን አሰናብቶ በይፋ መዘጋቱን አስታውቋል።
የትግራይ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ግን ለብሮድካስት ባለስልጣን ጥያቄ ዛሬ ምላሽ ሰጥቷል።
በትግራይ ክልል ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ በአቶ ብርሃኑ አባዲ ፊርማ በወጣው የደብዳቤ ምላሽ ላይ የሰኔ 16ቱ የአዲስ አበባውን የድጋፍ ሰልፍ ያልተላለፈበትን ምክንያት በዝርዝር አስቀምጧል።
በዋናነት ሰልፉ እንደሚካሄድ ቀድሞ ጥቆማ አልደረሰንም ያለው የትግራይ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት በጉዳዩ ላይ ለመወያየትም ሆነ ውሳኔ ለመስጠት አልቻልንም በማለት ያብራራል።
ሌላው በምክንያትነት የተጠቀሰው የሰማዕታት ቀን በሰኔ 15 የሚከበር በመሆኑ ለትግራይ ቴሌቪዥን ከዚህ ክስተት በልጦ ትኩረት የሚሰጠው ሌላ ጉዳይ ሊኖር ስለማይችል ሰፊ የአየር ጊዜ ለሰማዕታት ቀን ተሰጥቷል ይላል ደብዳቤው።
ከሰልፉ በኋላ የተፈጠሩትን ክስተቶች ግን ሽፋን ሰጥቼአለሁ በማለት የትግራይ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ለብሮድካስት ባለስልጣን በሰጠው ምላሽ ገልጿል።
ድርጅቱ ብሮድካስት ባለስልጣን አንድን የመገናኛ ድርጅት ለምን ዜና ወይም ዝግጅት አላስተላለፍክም ብሎ ለመጠየቅ የሚያስችለው ህጋዊ ሃላፊነት የለውም ብሏል።
ባለስልጣኑ ከትግራይ መገናኛ ብዙሃን ይልቅ ሌሎች የዕለቱን ሰልፍ የቀጥታ ሽፋን የሰጡትን የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችን ተጠያቂ ማድረግ ነበረበት በማለት ብሮድካስት ባለስልጣንን ወቅሷል።
በሰኔ 16ቱ ሰልፍ የኢፌድሪን ህገመንግስት የሚጻረሩ መልዕክቶች የተላለፉ መሆኑን የጠቀሰው የትግራይ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፡ ህጋዊ ያልሆኑ ሰንደቅ ዓላማዎች የተውለበለቡበት፡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጁ ድርጅቶች አርማዎች የታዩበት፡ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ መፈክሮች የተሰሙበት ሰልፍ ነበር ሲልም ገልጿል።
እንደነዚህ ዓይነት ህገመንግስቱን የሚጻረሩ ድርጊቶች የተፈጸሙበትን ሰልፍ ያስተላለፉ መገናኛ ብዙሃንም ቢሆን ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብሏል።
በተያያዘ ዜናም የትላንቱን የባህርዳር ትዕይንተ ህዝብ ጸረ ህገመንግስት ሲል የትግራይ ቴሌቪዥን መግለጹን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

No comments:

Post a Comment