(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 28/2010) በሶማሌ ክልል የሚፈጸመውን መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአስቸኳይ እንዲመረመር እንዲያደርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተጠየቁ።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄውን ያቀረበው ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው ድርጅት ነው።
ድርጅቱ በሶማሌ ክልል ስለሚፈጸሙ ሰቆቃዎች የሚያሳይ ጠለቅ ያለ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል።
በተለይም ጄይል ኦጋዴን በተሰኘው አሰቃቂ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ የሚፈጸምበት መሆኑን ምስክሮችን እማኝ በማድረግ አጋልጧል።
ዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስዎች ይፋ ያደረገው ሪፖርት በ88 ገጾች የተጠናቀረ ነው።
ሪፖርቱ ሰቆቃውን የሚፈጽሙ የጸጥታ ሃይሎች ኑዛዜን የሚያሳዩ በድብቅ የወጡ ቪዲዮዎችንና ድምጾችን ያካተተ መሆኑ ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ድርጅቱ ባለ 88 ገጹን ሪፖርት ያፋ ሲያደርግም ከ100 ሰዎች ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ መነሻ በማድረግ ነው።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በእስር ቤቱ ውስጥ እስረኞች ይደበደባሉ፣ይደፈራሉ፣እንዲዋረዱ ይደረጋል፣ህክምና እንያዳያገኙ የከለከላሉ፣ከቤተሰብ ጋር እንዳይገኛኑ ከማድረግ ጀምሮ በርካታ አሰቃቂ ድርጊቶች ይፈጸሙባቸዋል።
እስረኞቹ እንደሚሉት የእስር ቤቱና የልዩ ሃይል ሃላፊዎች እስረኞች እንዲሰቃዩ፣እንዲደፈሩና ምግብ እንዲከለከሉ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን ሴት በመድፈርና በማሰቃየቱ ሒደትም ተሳታፊ ናቸው ብለዋል።
በኦጋዴን ወህኒ/ጄይል ኦጋዴን/ ሕጻናት እንደሚወለዱ፣የሚወለዱትም በእስር ቤቱ ጠባቂዎች በተደፈሩ እስረኞች መሆኑንም ሪፖርቱ አጋልጧል።
ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከልም አንዱ “ሶስት አመት በጨለማ ቤት ቆይቻለሁ።ምሽት ላይ እወጣለሁ።የምወጣው ግን ብርሃን እንዳይ አይደለም ሊያሰቃዩኝ ስለሚፈልጉ ነው።የዘር ፍሬዎቼ በኤሌክትሪክ ይጠበሳሉ፣የሚጥሚጣ ዱቄት የተሞላበት የላስቲክ ከረጢት በጭንቅላቴ ውስጥ እንዳጠልቅ ያደርጋሉ፣ያ ሁሉ ስቃይ ሲፈጸምብኝ ደሞ አፌ ውስጥ ጨርቅ ተወትፎ ነው።”ሲል የስቃዩን ብዛት በምሬት ገልጾታል።
እስረኞቹን ለማዋረድም እራቁታቸውን ታሳሪ ጓደኞቻቸው ፊት ቆመው እንዲገረፉ ይደረጋል። ብድብደባ ሁለት ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ ሆነው ሕይወቱ ያለፈ እስረኛ መኖሩንም ሪፖርቱ አጋልጧል።
በሪፖርቱ ላይ እንደሰፈረው በአንድ ምሽት ብቻ 200 የሚሆኑ እስረኞች ላይ ውሃ እንዲደፋባቸው ይደረጋል።
ቀጥሎም አሰቃቂ የሚባል ስቃይ ከተፈጸመባቸው በኋላ ምንም ልብስ ሳይለብሱ ራቁታቸውን በአንድ እስር ቤት እንዲታጎሩ ተደርገዋል።
በአብዲ ኢሌ የሚመራው አስተዳደር በዋናነት እስረኞቹን ወደ ጄል ኦጋዴን ለማጎር ምክንያት የሚያደርገው ከኦብነግ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ነው።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህን አሰቃቂ ድርጊት ያጋለጠውንና በምስልና በድምጽ የተደገፈውን ማስረጃ ይፋ ካደረገ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚህ በዚህ አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ አስቸኳይ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
ድርጅቱ ይፋ ያደረገውን ሪፖርት መነሻ በማድረግም ታዛቢዎች አብዲ ዒሌንና አስተዳደሩን በዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ለመክሰስ በቂ ማስረጃ ነው ይላሉ ።
No comments:
Post a Comment