(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 11/2010) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 አመታት በኋላ የመጀመሪያውን መደበኛ በረራ ወደ አስመራ አደረገ።
ታዋቂ ሰዎችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሁለት ቡድን በሁለት አውሮፕላን ዛሬ አስመራ መግባቱም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም ላይ ከሚገኙ 50 ምርጥ አየር መንገዶች አንዱ መሆኑን ስካይትራክስ ትላንት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ከፈነዳበት ግንቦት ወር 1990 ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ ቀጥሏል።
ሐምሌ 1/2010 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የተመራውን ልኡክ የያዘ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አስመራ የገባ መሆኑ ይታወሳል።
ነገር ግን ይህ ጉዞ በቀጥታ ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የተደረገ ሳይሆን በጅቡቲ በኩል የተደረገ በረራ እንደነበርም ተመልክቷል።
የኤርትራ የአየር ክልል በይፋ መከፈቱን ተከትሎ ዛሬ አስመራ የገቡት 456
መንገደኞች መሆናቸው ታውቋል።
የመንገደኞቹ ጉዞም በሁለት አውሮፕላን መካሄዱም ታውቋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተጓዘውን ቡድን መምራታቸውም ተመልክቷል።
ድሪም ላይነር 787 በተባለው ቦይንግ አውሮፕላን ዛሬ ወደ አስመራ የተጀመረው ጉዞ በቀጣይ ወደ አሰብ በተለይም ወደ ምጽዋ ሊቀጥል እንደሚችልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በይፋ ወደ አስመራ የጀመረው በረራ የአየር መንገዱን መዳረሻዎች ወደ 115 ከፍ እንደሚያደርገውም ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአለም ላይ ያሉ አየር መንገዶችን አመታዊ ደረጃ የሚያወጣው ስካይትራክስ የሲንጋፖሩን ሲንጋፖር አየር መንገድን የአመቱ ምርጥ አየር መንገድ በማለት ሰይሟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድንም ከ50 ምርጥ አየር መንገዶች አንዱ ሲል ሪፖርቱን አውጥቷል።
ስካይትራክስ ትላንት ይፋ ባደረገው አመታዊ የአየር መንገዶች ደረጃ ሲንጋፖር አየር መንገድ፣ኤ ኤን ኤ የተባለው የጃፓኑ አየር መንገድ፣እንዲሁም ኤምሬትና ኢቫ ኤር አየር መንገዶች ከአንድ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
ከነሃሴ 2017 እስከ ግንቦት 2018 በ300 መቶ አየር መንገዶች ላይ በተካሄደውና የ105 ሃገራት ዜጎች በተሳተፉበት በዚህ ጥናት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ከአለም ደግሞ ከ50ዎቹ ደረጃ ላይ ስሙ ተቀምጧል።
ከግዙፎቹ የአሜሪካ አየር መንገዶች የአሜሪካን አየር መንገድና ዩናይትድ አየር መንገድን በመቅደም 40ኛ ደረጃን ይዟል።
ሌሎች የአሜሪካ አየር መንገዶች ዴልታና አላስካ 37ኛ 38ኛ ደረጃን በመያዝ በቅርብ ርቀት ቀድመውት ተገኝተዋል።
ከአፍሪካ አየር መንገዶች የደቡብ አፍሪካው ሳውዝ አፍሪካን አየር መንገድ 45ኛ፣የኬንያው አየር መንገድ ደግሞ 85ኛ ሆነዋል።
ጥናቱ ተጓዦች በአየር መንገዶቹ ላይ ያላቸውን እርካታ መሰረት ያደረገ መሆኑም ተመልክቷል።
No comments:
Post a Comment