Wednesday, July 11, 2018

ሲኖዶስን ወክለው ሶስት ጳጳሳት ወደ አሜሪካ ሊጓዙ ነው

Image may contain: sky, tree, house, cloud, plant and outdoor(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 4/2010) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አባቶች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በሽምግልና ለመፍታት ሶስት ጳጳሳት የሀገር ቤቱን ሲኖዶስ ወክለው ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙ ተገለጸ።
ፓትሪያሪክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ አባቶቹ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉዞ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ፓትሪያሪክ አቡነ መርቆሪዮስ ከሐገር በመውጣታቸው ላለፉት 26 ዓመታት የቤተክርስቲያኒቱ ምዕመናን ማዘናቸውንና ቤተክርስተያኒቱ በሰላም እጦት ውስጥ ማለፏን ገልጸዋል።
ከሐምሌ 11/2010 ጀምሮ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል በሚካሄደው የእርቅ ሒደት ላይ የሚሳተፉ ሶስት ሊቃና ጳጳሳት መወከላቸው
ተገልጿል።
በሳምንቱ መጨረሻ ወደ አሜሪካ ይጓዛሉ ተብሎም ይጠብቃል። ፓትሪያርክ ብጹእ አቡነ ማቲያስ አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ 26 አመታት ምዕመናኑን ያሳዘነውና ቤተክርስቲያኒቱንም ሰላም የነሳት የፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስና የሌሎች አባቶች ስደት በእርቅ ፍጻሜ እንደሚያገኝም እምነታቸውን ገልጸዋል።
ሰላሙን ለመመለስ ከ2003 አመተ ምህረት ጀምሮ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። በውጭ የሚገኘውና በፓትሪያርክ ብጹእ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራው ሲኖዶስም ለእርቅ ሒደቱ ያለውን ፍላጎት በግልጽ ማሳየቱንም ገልጸዋል።
የእስከዛሬዎቹ ጥረቶች ስልጣን ላይ ባለው መንግስትና በባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ሲከሽፉ መቆየታቸውም ሲገለጽ ቆይቷል።
በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ያለው የመንግስት ተጽእኖ እየቀነሰ በመምጣቱ በተለይም የሒደቱ ዋነኛ እንቅፋት የሚባሉት አቶ አባይ ጸሃዬ ሚናቸው በመገደቡና የእሳቸው መልዕክተኞችም ተሰሚነት በማጣታቸው የእርቅ ሒደቱ ፍጻሜ እንደሚያገኝ በሃገር ቤት ያሉ አንዳንድ ካህናት ከፍተኛ እምነት አሳድረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም አባቶቹ ችግራቸውን እንዲፈቱ በይፋ ጥሪ ማቅረባቸው የታወሳል።
በዋሽንግተን ቆይታቸውም ከፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ጋር እንደሚነጋገሩም መረዳት ተችሏል።
የሽምግልና ሒደቱ ፍጻሜ ካገኘም ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሪዎስና ሌሎቹ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
4ኛው ፓትሪያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ በመንግስት ጣልቃ ገብነት ከመንበራቸው ላይ እንዲነሱ መደረጉን የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ለአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ዶናልድ ያማማቶ መናገራቸው በዊክሊክስ በኩል ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ለአባቶቹ መከፋፈልና ለቤተክርስቲያኒቱ ሰላም ማጣት ምክንያት የሆነውን ደብዳቤ የፈረምኩት እኔ ነኝ በማለት መጸጸታቸውን ለአምባሳደር ያማማቶ የገለጹት አቶ ታምራት ላይኔ አባቶቹን ለማስታረቅ እንደሚሰሩም ቃል ገብተው ነበር።
ሆኖም ለአሜሪካው ዲፕሎማት የሰጡትን መግለጫ በሌላ መድረክ ሳይደግሙ ስለሽምግልናው ምንም ሳያነሱ ድምጻቸውን አጥፍተዋል።

No comments:

Post a Comment