(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 3/2010) ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አሕመድን በዋሽንግተን ዲሲ ለመቀበል በተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት አወቃቀር ላይ ማስተካከያ መደረጉ ተገለጸ።
በኮሚቴው አወቃቀር ላይ ማስተካካያ የተደረገው በአሰራሩ ላይ ከአባላቱ እና ከልዩ ልዩ ወገኖች የተነሳውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ መሆኑን አስተባባሪዎች ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ስራውን ከጀመረ አንድ ወር በሆነው የዋሽንግተን ዲሲ አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ በፊት ያልነበሩና የጠቅላይ ሚንስትሩን የለውጥ እንቅስቃሴ የሚቃወሙ ሰዎች እንዲገቡ መደረጉ ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።
የኮሚቴው ውክልናም ከዚህ ቀደም በአገዛዙ ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ያደረጉ የነበሩ ታዋቂ አክቲቪስቶችን ባለማካካተቱ ተቃውሞ አስነስቷል።
ይሕ በመሆኑም በኮሚቴው አወቃቀር ላይ ማስተካካያ እንደተደረገና በዚህ ሂደት መሳተፍ ለሚፈልጉ ታዋቂ አክቲቪስቶችም መድረኩ ክፍት መሆኑንን በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ማስተወቁ ይታወሳል።
ሰኔ 29/2010 በኢምባሲው የተሰጠው መግለጫ ጭግሮች እንደነበሩበት በማመን በሂደቱ ጉድለቶችን ለማስተካከል ዝግጁ መሆኑን በዋሽንግተን ዲሲ የጠቅላይ ሚንስትር ዶር አብይ አሕመድ አቀባበል ኮሚቴ አስተባባሪ ገልጿል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ እኢአ ሀምሌ 28 /2018 በዋሽንግተን ዲሲ በሚያደርጉት ውይይት 25 ሺህ ያህል ኢትዮጵያዊያን በኮንቬንሽን ሴንተር ይሳተፋሉ ተብሏል።
ይሕ ስብሰባ ያለምንም ክፍያ በነጻ የተጠራ ሲሆን መድረኩም ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ክፍት መሆኑ ተነግሯል።
በኋላ ላይ ግን 1 ሺህ 5 መቶ ከሚሆኑ የማህበረሰብ ተወካዮችና ታዋቂ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመለስተኛ አዳራሻ ሊኣላ ውይይት እንደሚደረግም ለማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment