Tuesday, July 10, 2018

የህወሃት አባላት ያልሆኑ የጦር ጀነራሎች በአስከፊ ኑሮ ውስጥ ናቸው ተባለ

Image may contain: 2 people, people sitting and outdoor(ኢሳት ዲሲ--ሐምሌ 3/2010) በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ማንነትን መሰረት ባደረገ የማግለል ርምጃ የህዉሐት አባላት ያልሆኑ የጦር ጀነራሎች ከሰራዊቱ ያለጡረታ እየተገፉ በአስከፊ ኑሮ ውስጥ ማለፋቸውን አንድ የጦር ጄኔራል ለኢሳት ገለጹ።
በተለያዩ የሰራዊቱ የግምገማ መድረኮች የሕወሃት የበላይነትን በተመለከተ የሚነሱ አስተያየቶች ዋጋ ሲያስከፍሉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር በመረጃ ዋና መምሪያ የትንተና እና ፕሮዳክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ብርጋዴር ጀኔራል መላኩ ሽፈራው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በመከላከያ ሰራዊቱ ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፣ በሥርዓቱ ውስጥ ያለውን ችግርና የብሔር አድልዎ በዝርዝር ተመልክተዋል።
የህዉሐት ታጋዮች በነበሩ የጦር ጀነራሎች መካከል ባለው የርስ በርስ ግጭትም እነ ጀነራል ሰዓረ መኮንን፣ በጀነራል ሳሞራ አማካኝነት ከደረጃ ዝቅ እንዲሉ የተደረገበትንም ሁኔታ አስታውሰዋል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር አሜሪካ ለስብሰባ መጥተው ሥርዓቱን ከድተው አሜሪካ ከቀሩ በርካታ ወራትን ያስቆጠሩት ብ/ጀነራል መላኩ ሽፈራው፣ ከሶስት ዓመት በፊት MI-35 ሒሊኮፕተር ይዘው ኤርትራ የገቡትን ፓይለቶች በተመለከተ ምርመራ እንዲያደርግ የተመደበው ቡድን ውስጥ በነበራቸው ተሳትፎ አብራሪዎቹን ወደዚያ ውሳኔ ያደረሳቸውን የምርመራ ውጤትም በዚሁ ቃለምልልስ አንስተዋል።
ከቅማንት እና ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተነሱ ግጭቶች ውስጥ የሕዉሐትም የብአዴን ነባር አመራርን ተሳትፎ እንዲሁም የመከላከያ የጦር አዛዦችን ሚና በቃለ ምልልሱ አንስተዋል።

ኮለኔል ደመቀ ዘውዱንና ሌሎች የወልቃይት ማንነት አስተባባሪ ኮሜቴ አባላትን ለማፈን ከአዲስ አበባና ከትግራይ የተላከው ቡድን ከአማራ ክልል መንግስት ዕውቅና ውጭ እንደነበርም የመከላከያ ሚኒስቴርን መረጃ ዋቢ በማድረግ አስታውሰዋል።
ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ በይፋከሚታወቀ የሐገሪቱ የደህንነት መዋቅር ወጭ እንደሚንቀሳቀስ የገለጹት ብርጋዴር ጄነራል መላኩ ሺፈራው ይህ የስውር መዋቅር ነጋዴዎችንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችንም እንደሚጨምር ገልጸዋል።
ይህ ቡድን በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ጭምር በመግባት የማፍረስ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ጄኔራል መላኩ ሽፈራው የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ሜቴክ እንዴት እንደተቋቋመና በኋላም ሙሉ በሙሉ የሕዉሐት የጦር መኮንኖች እጅ ወድቆ ግልጽ ዘረፋ የቀጠለበትን ሁኔታም በዝርዝር አስረድተዋል።
ጥያቄ ያነሱና አሰራሩን የተቹ የሌላ አካባቢ ተወላጆች እየተባረሩ አመረሩ በአንድአካባቢ ሰዎች እጅ ሙሉ በሙሉ እስከ መውደቅ የደረሱበትን ሁኔታ ዘርዝረዋል።
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ኣንቅስቃሴ አበረታችና ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የገለጹት ብርጋዴር ጀኔራል መላኩ ሽፈራው፣ በውጭ ሃገር የሚኖረውም ኢትዮጵያዊ ከለውጥ ሃይሎቹ ጎን እንዲሰለፍም ጥሪ አቅርበዋል።
ርሳቸውንም ወደ ሃገራቸው ተመልሰው የለውጥ ሃይሎቹን ለማገዝ ያላቸውንም ፍላጎትም አሳይተዋል።
በሕዉሃት ውስጥና በሰራዊቱ ውስጥ ባሉ የሕዉሃት አባላት ጭምር የለውጥ ሃይሎች ስለመኖራቸው ያላቸውን እምነት በዚሁ ቃለ ምልልስ አንስተዋል።
በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃና ዋና መምሪያ የትንተናና ፕሮዳክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከሆኑት ከብ/ጀነራል መላኩ ሽፈራው ጋር ኢሳት ያደረገውን ቃለ ምልልስ ከሰሞኑ ይዘን እንቀርባለን።

No comments:

Post a Comment