Monday, June 4, 2018

በጉጂና ጌዲዮ ብሄረሰቦች መካከል ጋብ ብሎ የቆየው ግጭት ለሶስተኛ ግዜ ዳግም አገረሸ።

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 27/2010) ትላንት ምሽት በተቀሰቀሰው ግጭት በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ወደ ሞያሌ የሚወስደው ዋናው መንገድ ገደብ የተሰኘች ከተማ ላይ በመዘጋቱ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መቋረጡ ታውቋል። እንደገና በተቀሰቀሰው ግጭት የደረሰው ጉዳት በዝርዝር ባይታውቅም በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥቃት መፈጸሙን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። በእስካሁኑ ግጭት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከ200ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። በርካታ ቤተክርስቲያናት ፈርሰዋል። ቡና መፈልፈያ ድርጅቶች፣ የንግድ ቦታዎችና ተሽከርካሪዎች ወድመዋል። በጉጂና ጌዲዮ ብሔረሰቦች መካከል ተቀስቅሶ የነበረውና ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ያስከተለው የእርስበእርስ ግጭት ከአንድ ወር ጋብ ማለት በኋላ ትላንት ምሽት በድጋሚ መቀስቀሱን ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች የገለጹት። ባለፈው አንድ ወርም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች መለስተኛ ጉዳት ያስከተሉ ግጭቶች እንደነበሩ ታውቋል። ሆኖም በሃገር ሽማግሌዎችና በግብረሰናይ ተቋማት ጥረት ግጭቱ እንዳይሰፋ ተደርጎ ቆይቷል። ትላንት ምሽት ግን ወደነበረበት ቀውስ መግባቱን የሚያሳዩ
መረጃዎች እየወጡ ነው። በተለይም የሁለቱ ወገኖች ግጭት ማዕከል በምትባለው ገደብ በተሰኘች ከተማ አቅራቢያ ከፍተኛ የሚባል ግጭት መከሰቱን ለማወቅ ተችሏል። ጋብ ብሎ የነበረው ግጭት ዳግም ያገረሸበት ምክንያት ለጊዜው አልታወቀም። በኢሳት የመረጃ ምንጮች ግምት ከ50 በላይ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። በሰው ህይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እየተጠበቀ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ግጭቱን በመሸሽ ወደ አቅራቢያ ጊዲዮ ዞን መንደሮች መሰደዳቸው ታውቋል። ከአዲስ አበባ ሞያሌ የተዘረጋው ዋና የትራንፖርት መስመር አቋርጦ በሚያልፍባት ገደብ ከተማ በግጭቱ ምክንያት መንገዱ እንደተዘጋም የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ መስሪያ ቤት ኦቻ በተያዘው ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው ሪፖርት ከምዕራብ ጉጂ ተሰደው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሸሹ ሰዎች ቁጥር ከ270 ሺህ በላይ ነበር። ድርጅቱ ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረገው እንቅስቃሴ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችን ዳግም የመመለስ ስራ መከናውኑ በመገለጹ አሁንም ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች በመጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ሆኖም ትላንት እንደአዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት የስደተኞቹን ቁጥር ወደነበረበት እንደሚመልሰው ተገምቷል። ዳግም ስለተቀሰቀሰው ግጭት በመንግስትም ሆነ በኦቻ በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም።

No comments:

Post a Comment