(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 27/2010) ከሀና ማርያም የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመሄድ አቤቱታ ሲያቀርቡ መዋላቸው ተገለጸ።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምረው፣ወደ ማዘጋጃ ቤትና አሜሪካን ኤምባሲ ዛሬም በድጋሚ ያመሩት ተፈናቃዮቹ፡ ቤተመንግስት ሲደርሱ ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በርካታ ተፈናቃዮች ከፖሊስ ጋር በነበረው ግጭት ጉዳት እንደደረሰባቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል ከቤንሻንጉል ጉምዝ የተፈናቀሉ ተጨማሪ 250 የአማራ ተወላጆች ወደ ባህርዳር በመጓዝላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። አንድ ወሩን የተሻገረው የሃና ማርያም ተፈናቃዮች እሮሮ ዛሬ ፈንቅሎ ወጥቷል።
ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑ አባዎራዎች ልጆቻቸውን ይዘው ለአቤቱታ በቅድሚያ ያመሩት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ነበር።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ወደ ቤተመንግስት ሄደው በፖሊስ ተደብድበው የተመለሱት የሀና ማርያም ተፈናቃዮች ተስፋ አልቆረጡም ዛሬም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ አመርተዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እንደሚሉት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ቢሄዱም ያናገራቸው አንድም የመንግስት ባለስልጣን የለም።
ቀጥሎ ያመሩት ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ነበር። በዚያም ምላሽ የሚሰጥ የመንግስት ሃላፊ አላገኙም።
የደረሰባቸውን በደልና ጉዳት የሚያስተካክልላቸው ይቅርና የሚሰማቸው ያጡት ተፈናቃዮች ሽሮ ሜዳ ወደ ሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ማምራታቸውን ነው ያነጋገርናቸው የገለጹት።
ባለፈው ሳምንትም በተወሰኑ ተወካዮቻቸው አማካኝነት የአሜሪካን ኤምባሲን ለማነጋገር ሙከራ ማደረጋቸውን የሚገጹት ተፈናቃዮች በሀገር ቤት መኖር አትችሉም ከተባልን የአሜሪካ መንግስት ጥገኝነት ይስጠን የሚል ጥያቄ ይዘው መቅረባቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም በአሜሪካን ኤምባሲም ጥያቄያቸውን የተቀበላቸውም ሆነ ያነጋገራቸው አካል የለም። በፖሊስ አማካኝነት ከአካባቢው እንዳይጠጉ መደረጋቸው ታውቋል።
በመጨረሻም ወደ ቤተመንግስት ማምራታቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው። በከፍተኛ ቁጣና ቁጭት ውስጥ ሆነው ወደ ቤተመንግስት ያመሩት ተፈናቃዮቹ በተለምዶ እሪ በከንቱ በሚባለው አካባቢ ሲደርሱ በፖሊስ ገደብ እንዳያልፉ ተደርገዋል።
መንገዱን አጥሮ የጠበቃቸው ፌደራል ፖሊስ የተፈናቃዮቹን ግስጋሴ በመግታት ያስቆማቸው ሲሆን የተወሰኑት ላይም ድብደባ መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል።
ተፈናቃዮቹ የሚሰማን አካል ከሌለ ወዴት ሄደን አቤት እንበል ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ። ከአንድ ወር በላይ ተንከራተትን፣ ህጻናት ልጆቻችን ከትምህርታቸውም ተፈናቅለው ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው የሚሉት ተፈናቃዮች ዜጎች ካልሆንን ወደሌላ ሀገር በጥገኝነት ያስረክቡን ሲሉም በምሬት ይናገራሉ።
ኢሳት ጉዳዩን በተመለከተ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለከተማንም ሆነ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
በሌላ በኩል ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገልጿል።
ዛሬም ከ250 በላይ የአማራ ተወላጆች የጃዊን በረሃ አቋርጠው ወደ ባህርዳር በማምራት ላይ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አሰቃቂ በሆነ መልኩ ግድያ እየተፈጸመባቸው መሆኑን የሚገልጹት የአማራ ተወላጆቹ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ህይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ መሰደዳቸውን ይናገራሉ።
በቤንሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እንዲቆም ከየአቅጣጫው ተቃውሞ እየቀረበ ቢሆንም ጥቃቱም መፈናቀሉም መቀጠሉን ነው የኢሳት የመረጃ ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ የተቻለው።
No comments:
Post a Comment