Thursday, June 7, 2018

የድሬደዋ ከተማ ነዋሪዎች ለስደት እየተዳረጉ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 30/2010) የድሬደዋ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ የመኖር መብታቸው በመገፈፉ ለስደት እየተዳረጉ መሆኑ ተገለጸ።ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ምርጫ 97ን ተከትሎ የተተገበረው 40፣40፣20 ፖለቲካ በከተማዋ ተወልደው ያደጉ ዜጎችን መብት ገፏል ሲሉም ተናግረዋል።ድሬደዋ ተወልደው አድገው የማይኖሩባት ከተማ ሆናለች ሲሉ ነዋሪዎቹ ምሬታቸውን ይገልጻሉ።
የከተማዋ ነዋሪዎች የድሬደዋ የፍቅር ከተማነት ጥያቄ ውስጥ የገባው ኢሕአዴግ ምርጫ 97ን ተከትሎ በ1999 በከተማ ውስጥ ቢሮውን መከፈቱ ነው ይላሉ።
የቢሮውን መከፈት ተከትሎ ደግሞ ምንም አይነት እውቅናና ድጋፍ የሌለውና በቻርተሩም የማይደገፍ 40፡40፡20 የሚባል ፖለቲካ መተግበር ጀመረ።

ይሄ አሰራር ሲተገበርም ዋነኛ አላማው በሶማሌና አማራ ክልል ተወላጆች መካከል ያለውን ይገባኛል ጥያቄ ማርገብ የሚል ነበር ይላሉ።
በከተማዋ ያለውን ተጠቃሚነትም 40 በመቶ ለሶማሌ፣40 በመቶ ደግሞ ለኦሮሞ ተወላጅ ይሰጥና ቀሪውን 20 በመቶ ደግሞ ለሌላው የከተማዋ ተወላጅና ነዋሪ ይተዋል።
ይሄ አተገባበር አብዛኛውን ሕዝን ያላካተተና የከተማ አስተዳደሩንም መመሪያ ከግምት ያላስገባ ነው ሲሉ ይከሳሉ።
ኢሕአዴግ ቢሮውን በከተማ አስተዳደሩ ሲከፍትም የድሬደዋ ቻርተር የሚደነግገውን የስራ ቋንቋ አማርኛ ነው የሚለውን አሰራር ሰረዘው ያላሉ።
እንደ ነዋሪዎቹ አባባል ያንን ተከትሎም በተለያዩ ሙያዎች ሰልጥነው ስራ የሚፈልጉ ወጣቶች ሶማሊኛና ኦሮምኛ ቋንቋ የማይችሉ ከሆነ የስራ እድል አያገኙም።
ይሄ አሰራር በራሱ በወቅቱ ይፋ ከሆነው የቤትና የሕዝብ ቆጠራ መረጃ ጋር የሚጣረስ መሆኑንም ይናገራሉ። በሰአቱ ይፋ የሆነው የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንደሚያመለክተው ከሆነ ሶማሌ 13.9 በመቶ ፣ኦሮሞ 48 በመቶ ሲሆን የአማራው ቁጥር ደግሞ 27.7 በመቶ ነበር።
ነገር ግን በወቅቱ በአቶ አባይ ጸሃዬ ውሳኔ መሰረት 40 በመቶ የምክር ቤት ወንበርና የሃላፊነት ቦታዎችን የሶማሌ ክልል እንዲይዝ 40 በመቶውን ደግሞ የኦሮሞ ክልል እንዲይዝ ተደረገ።
በቁጥር ከሶማሌ ክልል በላይ የሆኑት የአማራ ተወላጆችም ከሌሎች ብሔሮች ጋር 20 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው መደረጉን ነው የሚናገሩት።
ሌላው የከተማዋ የልማት ማነቆ ሆኖ የቆየው ደሞ በእኚሁ በአቶ አባይ ጸሃዬ ትዕዛዝ መሰረት ከተማዋ በፈረቃ እንድትተዳደር መወሰኑ ነው።–ሁለት አመት በሶማሌ ሁለት አመቱን ደሞ በኦሮሚያ ክልል።
የከተማዋ ነዋሪዎች ይሄ አሰራር ይወገድልን የሁላችንም የነበረችውን የፍቅር ከተማዋን ድሬዳዋን መልሱልን ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

No comments:

Post a Comment