(ኢሳት ዜና ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ባለፈው እሁድ ያገረሸውን ግጭት ተከትሎ ዛሬም የዜጎች ህይወት እያለፈ ነው። በርካታ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶችም ወድመዋል። በኦሮምያና ደቡብ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተለይም በባንቆ ጎትቲ፣ በባንቆ ላሌሳ፣ በባንቆ ጣጣጡ፣ በደገብ ኤደራ፣ በከቾሬ ወረዳ በስቄ፣ በቶሬ እና ሽፎ አከባቢዎች ግጭሬ ቀጥሏል። በባንቆ ጣጣቱ አካባቢ ከአንድ ቤተክርስቲያንና ከአንድ የመንግስት ትምህርት ቤት ውጭ ከተማው በቃጠሎ መውደሙን የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ። በባንቆ ጎትቲ 3 ሰዎች፣ በኮቾ ወረዳ ሃልጨብ በተባለ ስፍራ የቀበሌው ሊቀመንበር ተገድሏል። ሁለት የመከላከያ ሰራዊት አባላትም መሞታቸው ተነግሯል። በባንቆ ጣጣቱም አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ህይወቱ ሲያልፍ አንድ ሌላ ወታደር ደግሞ በዲላ ሪፈራል ሆስፒታል መተኛቱን፣ አንድ መምህርም በሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት በላኩት መረጃ አመለክትዋል። በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። በጉጂ በኩል ያሉ ሰዎችን ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም። የኦሮምያም ሆነ የደቡብ ክልል ባለስልጣናት በግጭቱ ዙሪያ የሰጡት መግለጫ የለም።
No comments:
Post a Comment