Wednesday, June 20, 2018

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ አንድ የልኡካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ አስታወቁ

(ኢሳት ዜና ሰኔ 13 ቀን 2010 ዓ/ም) ፕሬዚዳንቱ ይህን የተናገሩት በየዓመቱ በሚከበረው የሰማዕታት መታሰቢያ ዝግጅት ላይ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ባደረጉት ንግግር ነው። ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ አዲስ ትብብር ለመመስረት ምቹ ነው ብለዋል። ህወሃት የውጭ ሃይሎችን አጀንዳ ለማራመድ ባደረገው ጥረት በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት መቀስቀሱን የተናገሩት አቶ ኢሳያስ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ጥፋት ህዝቡ ለአመጽ እንዲነሳና የህወሃት ሴራ ፍጸሜ እንዲያገኝ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል። የህወሃት መሪዎች አገዛዛቸው እንዳበቃ ቢረዱትም፣ አሁንም ስልጣናቸውን ለማቆየት ከኤርትራ ጋር ያለው ውጥረት እንዲቀጥል ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ስልቶችን ይጠቀማል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ከእነዚህ ስልቶች አንዱ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንዳይሰፍን ማድረግ ነው ብለዋል። አገራቸው ይህንን መንገድ ለመዝጋትም ማሰቡዋንም ተናግረዋል። ህወሃት በሁለቱ አገራት መካከል የረጨው የጥላቻ መርዝ በቀላሉ ሊጠፋ እንደማይችልም አቶ ኢሳያስ አክለው ገልጸዋል። ዶክተር አብይ አህመድ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያን መንግስት የእርቅና ድርድር ጥሪ ለሰጡት ምላሽ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የኤርትራን የልዑካን ቡድንን በታላቅ አክብሮት ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ ናት ብለዋል። የኤርትራ የሰጠቸው
መልስ በአካባቢው የቆየውን ውጥረት የሚያረግብና በካባቢው አገራት መካከል ያለውን ውጥረት የሚቀንስ ተድርጎ ተወስዷል። የአሜሪካ እና የተለያዩ አረብ አገራት ዲፕሎማቶች ሁለቱን አገራት ለማስታረቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ የዲፕሎማቲክ ዘመቻ መክፈታቸው ይታወቃል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዲፕሎማቲክ ልኡካንን ወደ አዲስ አበባ ለመላክ መወሰናቸው ከአዲሱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ለመመስረት ማሰባቸውን ያሳያል። አቶ መለስዜናዊ እና አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ወደ አስመራ ሄደው ለመደራደር ዝግጁ ነን እያሉ ሲገልጹ ቢቆዩም አልተሳካለቸውም ነበር።

No comments:

Post a Comment