(ኢሳት ዜና ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ/ም) የህወሃት ደህንነቶች አንድ የአብዲ ኢሌን ተቃዋሚ ለመያዝ ያደረጉት ሙከራም ሳይሳካላቸው ቀርቷል በአብዲ ኢሌ ፍጹማዊ አገዛዝ የተማመሩ ከውጭ አገር ወደ አገር ቤት የተመለሱ እንዲሁም በክልሉ የሚኖሩ የአገር ሽማግሌዎች ከጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ ባለመሳካቱ ዛሬ በቤተመንግስት ዙሪያ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። የህወሃት ነባር አመራሮች ሽማግሌዎችን ከአብዲ ኢሌ ጋር ለማስታረቅ ያደረጉት ሙከራ ከከሸፈ በሁዋላ፣ የሽማግሌዎችን ህይወት አደጋ ውስጥ የሚጥል እርምጃ በህወሃትና በአብዲ ኢሌ አቀናባሪነት እየተፈጸመ መሆኑ ሰልፉን ለማድረግ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗቸዋል። ትናንት ምሽት የህወሃትና የአብዲ ኢሌ የደህንነት አባላት ከተቃዋሚዎች መካከል አንዱ የሆኑትንና አረን በተባለው ሆቴል አርፈው የነበሩትን አሊ ገዓንን አፍነው ለመውሰድ ሙከራ አድርገዋል። አቶ አሊ የቀድሞው የተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ። ግለሰቡ በአሁኑ ሰዓት ወረዳ 17 ፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙና ወደ ጅጅጋ አለመሄዳቸው ታውቋል። ባለፈው ሳምንትም እንዲሁ የአብዲ ኢሌ ተቃዋሚ የሆኑትን አቶ ኸደር ጅግሬን ለማፈን የተደረገው ሙከራ በአዲስ አበባ ፖሊስ ፣ በደህንነት መሥሪያ ቤትና በአሜሪካ ኤምባሲ አማካኝነት ከሽፎ እንደነበር መዘገቡ ይታወቃል ፡፡
No comments:
Post a Comment