(ኢሳት ዜና ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ/ም) በሃረር ከተማ ሃኪም ወረዳ ለኢንቨስተር የተሰጠውን መሬት አርሶአደሮች አናሳጥርም በማለታቸው 9 ሰዎች በልዩ ሃይል አባላት በተተኮሰ ጥይት ቆስለዋል። ህዝቡ ተቃውሞውን በማሰማቱ ቦታው እንዳይታጠር አስደርጓል። በተቃውሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት እህት ያሰራቸው ፎቅ ቤት በድንጋይ ተመቷል።። በአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጆች የሚኖሩባቸው ሶፊ ፣ ድሬ ጠያራና የረር ወረዳዎች የሃረሪ ክልል መብታቸውን ሊያስከብርላቸው እንዳልቻለ በመግለጽ ወደ ኦሮምያ ክልል እንዲጠቃለሉ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በእነዚህ ወረዳዎች የኦህዴድ አርማዎች እየተሰቀሉ ነው። በሃብሊና በኦህዴድ መካከል ያለው ውዝግብ መቀጠል በቅርቡ ክልሉን ለሚጎበኙት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ተጨማሪ ፈተና ይሆንባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ካሊድ በተባለ በአንድ የሃረሪ ባለስልጣን ወንድም ቤት ውስጥ ተቀጥራ ትሰራ የነበረችው የ13 አመት ታዳጊ ጉዳይ አሁንም የክልሉ ህዝብ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል። ከበደኖ ወረዳ የመጣችው የጫልቱ አብዲ በግዳጅ ከተደፈረች በሁዋላ ደፋሪዋ በብልቷ አካባቢ አሲድ ደፍቶ እንድትቃጠል አድርጓታል። ደፋረው ግለሰብ “እኔ ባለስልጣን ነኝ ብትናገሪ ምንም ነገር አታመጭም በማለትና በሰውነቷ ላይ የሚፈላ ውሃ እንደፈሰሳበት አስመስላ እንድትናገር አልያ እንደሚገድላት እንደዛተባት የገለጸው ወኪላችን፣ ክልሉ በስውር 2 ፖሊሶችን መድቦ ሰዎች እንዳይጎበኙዋት ማስደረጉም በመጨረሻም ከ4 ቀናት በሁዋላ ዘመዶቿ ለምስራቅ ሃረርጌ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አሳውቀው ታዳጊዋ እንድትተርፍ አድርገዋል። ጀጉላ ሆስፒታል የተኛቸው ታዳጊ ወጣት ጫልቱ ከማደንዘዢያ ስትነቃ የደረሰባትን ሁሉ ለህዝብ መናገሯ ታውቋል። ካሊድ የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ቢውልም፣ ማታ ማታ ቤቱ እያደረ ቀን ቀን ብቻ ለይስሙላ በእስር ቤት እንደሚታይ ወኪላችን ገልጿል። ታዳጊዋ ወደ ጥቁር አንበሳ ተልካ ህክምና እየተከታተለች ነው። ጉዳዩ በአገሪቱ ቴሌቪዥኖች እንዳይተላለፍ የክልሉ መንግስት ደብዳቤ መጻፉንና ተጽዕኖ እያደረገ መሆኑን ወኪላችን አክሎ ገልጿል።
No comments:
Post a Comment