(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 12/2010) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አግልግሎት ከፖለቲካ ወገኝተኝነት ተላቆ ሕዝብን የሚያገለገል ተቋም እንደሚሆን አዲሱ የተቋሙ ዋና ዳየሬክተር ገለጹ።
በቅርቡ በጠቅላይ ሚንስትር አብየ እህመድ የተሾሙት የቀድሞው የአየር ሐይል አዣዥ ጄኔራል አደም መሀመድ እንደገለጹት ተቋሙ የተጣለበትን ተልዕኮ ለመወጣት ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ በመደራጀት ማሻሻያ ይደረግበታል።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ትናንት ለፓርላማው ባደረጉት ገለጻ ደሕንነትና መከላከያው የፖለቲካ ወገንተኞችና የአፈና መሳሪያ ሆነው መቆየታቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
ጄነራል አደም መሃመድ አዲሱ የብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር ትውወቅ አድርገዋል።
በሰነ ስርአቱም ጄነራል አደም ሕገመንግስታዊ ስርአቱን ከአደጋ መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል ። ተቋሙ ተልዕኮውን ለማስፈጸም ከፖለቲካ ወገንተኝነት መላቀቅ ይኖርበታልም ነው ያሉት — ጄነራል አደም መሀመድ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል።
በአደባባይና በመገናኛ ብዙሃን ምስላቸው ሳይታይ ለረጅም አመታት የቆዩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሃላፊነት ቢነሱም በጡረታ ይገለሉ ወይንም ሌላ ቦታ ይመደቡ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
አቶ ጌታቸው አሰፋ በምዝበራና በርካታ ሰዎችን በመግደል እንዲሁም በማሰቃየት ይታወቃሉ።–ልጆቻቸውንም በውጭ ሃገራት በውድ ዋጋ እያስተማሩ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር መከላከያና ደህንነት ከገዥው ፓርቲ ፖለቲካ ያልተላቀቁና ወገንተኛ ሆነው ሲሰሩ እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ ግድያዎች አፈናዎችና ሰቆቃዎች ዋነኛ ፈጻሚ በመሆኑ በተለያዩ ወገኖች ሲወገዝ ቆይቷል።
የመከላከያ ሰራዊትም በተለያዩ ግድያዎች ተሳታፊ ነበር። በቅርቡ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከሃላፊነት ሲነሱ የመከላከያ ኢታማዦር ሹም የነበሩት ጄኔራል ሳሞራ የኑስም ከቦታቸው ተነስተው በሕወሃቱ ጄኔራል ሳእረ መኮንን መተካታቸው አይዘነጋም ።
ጄናራል ሳሞራ የኑስና አቶ ጌታቸው አሰፋ በስልጣን ዘመናቸው ስምምነት ሳይኖራቸው አንዱ ለአንዱ የጠላትነት ስሜት ይዘው መቆየታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment