(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 8 /2010) በሽብር ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው 300 ያህል እስረኞች እንዲፈቱ ተወሰነ።
መንግስት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት እስረኞቹ ከዛሬ ጀምሮ ከወህኒ ቤት እንደሚወጡም ተመልክቷል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው በይቅርታ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው እስረኞች በአጠቃላይ 304 ሲሆኑ ፣ከነዚህ ውስጥ ከአስራ አምስቱ በቀር ሁሉም የአሽባሪነት ክስ ተመስርቶባቸው የተፈረደባቸው ናቸው።
አበበ ካሴ እና ከለንደን ሄዶ አዲስ አበባ ላይ የታሰረው አበበ ወንድም አገኝ እንዲሁም ጥላሁን አበጀ ከተፈቱት ውስጥ ይገኙበታል።
በአጠቃላይ በአሽባሪነት ተከሰው ተፈርዶባቸው እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው 289 እስረኞች ዘጠኙ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው መሆናቸውም ተመልክቷል።
እስረኞቹ ከዛሬ ጀምሮ ከወህኒ ቤት እንዲወጡ የተወሰነ ሲሆን ፣ከተፈቺዎቹ ውስጥ ሶስት የኬኒያ ዜጎች እንደሚገኙበትም የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በተመሳሳይ ሌሎችንም እስረኞች የመፍታቱ ሂደት እንደሚቀጥልም ከመንግስት ኮሚኒኼሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መግለጫ መረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ተከትሎ በኢሕአዴግ ውስጥ ብቅ ያለው የለውጥ ሃይል ባደረገው ግፊት ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች፣ጋዜጠኞች ፣ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንዲሁም አክቲቪስቶችና ሌሎች በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ከየካቲት ወር ጀምሮ መፈታታቸው ይታወቃል።
መንግስት ከፌደራል ወህኒ ቤት በቅርቡ የተፈቱ እስረኞች ቁጥር 1105 መሆኑንም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ጅቡቲ ዛሬ 45 ኢትዮጵያውያንን ከወህኒ ቤት መፍታቷን አስታውቃለች።
No comments:
Post a Comment