(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 22/2010) በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ ያልታወቁ ሃይሎች 4 የፖሊስ አባላትን አቁስለው መሰወራቸው ተሰማ።
የገዳዮቹን ማንነት ለማወቅና ለፍርድ ለማቅረብ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን የኦሮሚያ መንግስት አስታውቋል።
የኦሮሚያ የገጠርና የፖለቲካ አደረጃጀት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በአካባቢው ያለው ሕዝብ እራሱን ከአጥቂዎች እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል የነበረው ግጭት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጋብ ቢልም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን መጠነኛ ግጭት ይታያል።
ግጭቱ ተባብሶ ይታይባቸው የነበሩት የምዕራብ ጉጂና ጌዶ አካባቢ የሶማሌና አዋሳኝ አካባቢዎች ባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንዲሁም በሞያሌ የነበረው ግጭት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ተሸጋግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በኦሮሚያ ያለው ግጭት ጋብ ቢልም በደቡብ ክልል በቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳና ሌሎች አካባቢዎች ግን ብሔር ተኮር ግጭቶች ነበሩ።
ሰሞኑን በተሰማው ዜናም በአሶሳ 10 ሰዎች ተገድለው ከ38 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ ደግሞ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች 4 ፖሊሶችን አቁስለው መሰወራቸው ተነግሯል።
የኦሮሚያ ክልል የገጠርና የፖለቲካ አደረጃጀት ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የፖሊስ አባላቱን ያቆሰሉትን ሰዎች ለመያዝ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
እናም ሕዝቡ የራሱን ጸጥታ ለመጠበቅ የበኩሉን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የፖሊስ አባላቱ ቆስለዋል ከመባሉ ውጪ አሁን ስላሉበት ሁኔታ የታወቀ ነገር የለም።
በኦሮሚያ ክልል ባለፈው ጊዜ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ስራ አስኪያጅ በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በናይጄሪያው ባለሃብት በኦሮሚያ ክልል የተቋቋመው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሰራተኞች ጋር በተፈጠረ ችግር የኩባንያው ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሕንዳዊና ኢትዮጵያዊት ጸሃፊያቸው መገደላቸው አይዘነጋም።
No comments:
Post a Comment