Monday, July 2, 2018

ዶክተር ካሳ ከበደ ኢትዮጵያ ገቡ

Image may contain: 1 person(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 25/2010) በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ በተለያዩ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት ዶክተር ካሳ ከበደ በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያ ገቡ።
የኢሕአዴግ መንግስት በ1997 በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን ግድያ በመቃወም ስራና ስልጣናቸውን ትተው ኤርትራ የገቡት ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋም በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ከረጅም አመታት ስደት በኋላ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ታውቋል።
ቅዳሜ ማለዳ አዲስ አበባ የደረሱት ዶክተር ካሳ ከበደ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በኢትዮጵያና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውም ታውቋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ይወያያሉ ተብለው የሚጠበቁት ዶክተር ካሳ ከበደ በኢትዮጵያ ለአጭር ቀናት ብቻ እንደሚቆዩም የቅርብ ምንጮች ገልጸዋል።

ዶክተር ካሳ ከበደ በቀድሞው የደርግ መንግስት ውስጥ በሚኒስትርነትና በአምባሳደርነት ያገለገሉ ሲሆን ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ከወጣ በኋላ ለ27 አመታት በስደት ቆይተዋል።
በስደት ቆይታቸው በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ሒደት ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተመልክቷል።
የሞረሽ ወገኔ መስራች አቶ ተክሌ የሻውም ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ ከተባባሪው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች ጋር እሁድ እለት አዲስ አበባ ገብተዋል።
በምርጫ 1997 በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ ሃላፊነታቸውን ጥለው ወደ ኤርትራ የተጓዙት ብርጋዴር ጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ እሁድ አዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ደጋፊዎቻቸው አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ከጄኔራል ሃይሉ ጎንፋ ጋርም የተባበሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮች በተመሳሳይ ሃገር ቤት ገብተዋል።

No comments:

Post a Comment