(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 25/2010) አልጄሪያ ባለፉት 14 ወራት ከ13 ሺ በላይ ስደተኞችን በኒጀር በረሃ ላይ እንዲጣሉ ማድረጓን አዲስ የወጣ አንድ ሪፖርት አመለከተ።
የአሶሼትድ ፕሬስ ሪፖርተርን ዋቢ አድርጎ የወጣው ሪፖርት በአብዛኛው በበረሃው እንዲጣሉ የተደረጉት ስደተኞች አልጄሪያን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ጥረት የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት ሜዲትራኒያንን አቋርጠው አውሮፓ የሚገቡ ስደተኞች ላይ ጫና ማድረጉን ተከትሎ በአካባቢው እየደረሰ ያለው ሰብአዊ ቀውስ መባባሱን ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት።
የአሶሺየትድ ፕሬስ ሪፖርተርን ዋቢ አድርጎ የወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአልጄሪያ ደቡባዊ ግዛት ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ስደተኞቹ በበረሀ እንዲያቋርጡ እንደሚደረጉና ቀናት በሚወስደው በዚህ ጉዟቸው ብዙዎች ለሞት እንደሚዳረጉ ተዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነም በ14 ወራት ውስጥ ብቻ ከ13 ሺ በላይ ስደተኞች በኒጀር በረሃ ውስጥ እንዲጣሉ መደረጋቸውም ሪፖርቱ አጋልጧል።
ኤን ፒ አር የተሰኘው ሬዲዮ በስፍራው የተገኘችውን የአሶሼትድ ፕረስ ጋዜጠኛን አንጋግሮ እንዳሰፈረው ሪፖርት ከሆነ ስፍራው እስከ 120 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚደርስ ሙቀት ያለበት መሆኑንና ማረፊያ ቦታ እንኳን የሌለው ምድረበዳ ነው።
ሪፖርተሯ በስፍራው ተገኝታ ያየቻቸው ስደተኞችም በድካምና በውሃ ጥም የተጎዱ መሆናቸውን በመግለጽ የአይን እማኝነቷን ገልጻለች።
ብዙዎቹ ስደተኞች ከምእራብ አፍሪካ የመጡ እንደሆኑ የገለጸችው የአሶሼትድ ፕረስ ዘገቢ ከስደተኞቹ መካከል ሴቶችና ህጻናትን መመልከቷን ገልጻለች።
ጋዜጠኛዋ አክላም ስለስደተኞቹ የአልጄሪያ መንግስትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ምንም ምላሽ አለማግኘቷን በሪፖርቱ ላይ አስፍራለች።
No comments:
Post a Comment